loading
ዲዲዬ ድሮግባ አፍሪካን በጋራ ሆነን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል አለ

ዲዲዬ ድሮግባ አፍሪካን በጋራ ሆነን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል አለ

 

አይቮሪኮስታዊው የቀድሞ የቼልሲ እና የአይቮሪ ኮስት ኮከብ ዲዲዬ ድሮግባ በአፍሪካ የቢዝነስ እና ጤና ፎረም ጋባዥነት በአዲስ አበባ ሀያት ሆቴል በመገኘት አፍሪካ ውስጥ በማህበራዊ እና ጤና ዘርፎች እየሰራ የሚገኘውን ስራ አብራርቷል።

ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር የተወያየው ድሮግባ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የገጠመው አቀባበል ፍፁም ያልጠበቀው እንደሆነ ተናግሯል። ” እዚህ ስመጣ የመጀመርያዬ ነው። ነገር ግን እጅግ ብዙ አፍቃሪ እንዳለኝ ተረድቻለሁ ” ብሏል።

ድሮግባ ጨምሮም ” አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አሁን ላይ የመደመጥ እና የመታየት እድል አላት። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተበታተንን ልጆቿ አቅማችንን አጎልብተን፣ ተምረን፣ ሰልጥነን እና ሰርተን ተመልሰናል፤ አሁን በጋራ ሆነን አፍሪካን ተባብረን አይዞሽ ልንላት እና ልንገነባት ይገባል። በጋራ ከሆንን የማንችለው ነገር የለም ” ሲል በጋራ የመስራት አስፈላጊነትን ገልጿል።

ከእግር ኳስ ራሱን ካገለለ በኋላ ራሱ ባቋቋመው ፋውንዴሽን አማካኝነት በትምህርት እና ጤና ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሆነ የተናገረው ድሮግባ በሀገሩ ትምህርት ቤት ከፍቶ ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል የትምህርት አሰጣጥ እንዲሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ የእናቶች እና ህፃናት ጤና ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጿል።

ወደፊትም በትምህርት እና ጤና ላይ ይበልጥ አተኩሮ መስራት እንደሚፈልግ የገለፀው ዲዲዬ ድሮግባ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚቻለው እንደ አንድ ሆኖ በትብብር በመስራት እንደሆነ ተናግሯል።

መረጃው የሶከር ኢትዮጵያ ድረ ገፅ ነው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *