loading
ዛሬ ምሽት በቻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር ዩናይትድ ከባርሴሎና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው የሚከናወኑ ይሆናል፡፡

በኦሌ ጉናር ሶልሻዬር የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም የስፔኑን ባርሴሎና ምሽት 4፡ 00 ሲል ያስተናግዳል፡፡

የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንት ዤርማ በድራማዊ ክስተት ጥሎ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ቀያይ ሰይጣኖቹ ፤ በአጥቂያቸው ማርከስ ራሽፈርድ የመሰለፍ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን ባይችሉም ተስፋ አድርገዋል፡፡ ኒማኒያ ማቲችም ቢሆን ለጨዋታው ብቁ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

የላንክሻየሩ ቡድን ትልቁ ስጋቱ የሊዮኔል ሜሲ ጉዳይ ሲሆን ተጫዋቹን ለማቆም ትልቁ የኦሌ ራስ ምታት ነው፡፡

ሜሲ በተያዘው የውድድር ዓመት በ40 ጨዋታዎች 43 ጎሎችን በተቃራኒ ቡድኖች መረብ ላይ ማስቆጠሩ እና ወቅታዊ ብቃቱ ከፍተኛ መሆኑ ደግሞ ለተጨዋቹ የሚደረገውን ቁጥጥር አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በቻምፒዮንስ ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ መገናኘት የቻሉት በ2011 የፍፃሜ ጨዋታ ሲሆን ያኔ ባርሳ 3 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ደግሞ የጣሊያኑ ክለብ ዩቬንቱስ ወደ አምስተርዳም ተጉዞ በዩሃን ክራይፍ አሬና አያክስን ይገጥማል፡፡

እንደ ዩቬ አሰልጣኝ ማሲሚሊያኖ አሌግሪ ገለፃ ጉዳት ላይ የነበረው ክርሲቲያኖ ሮናልዶ ተሰላፊ ተጫዋች ይሆናል፡፡ ጆርጂዮ ኬሌኒ እና ኢምሪ ካን በጨዋታው እንደማይኖሩም ተነግሯል፡፡

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ዋንጫ እና ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ለዘጠንኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ከ2004 በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡   

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *