loading
በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የደኅንነት ማረጋገጫ መሰጠቱ ተገለጸ::

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በሚመለከት ለፌደራል መንግሥት የደኅንነት ዋስትና ደብዳቤ መላካቸው ተነግሯል፡፡ ይህ የተገለጸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች እና ከምዕራባውያን አምባሳደሮች ጋር በመቐለ ከተገናኙ በኋላ መሆኑን ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ዘግቧል። በዚህም መሠረታዊ አገልግሎቶቹን መልሰው ሥራ ለማስጀመር ለጥገና ወደ ትግራይ ክልል ለሚሰማሩ ሠራተኞች የደኅንነት ዋስትና እንደሚሰጥ የሚገልጽ ደብዳቤ በዲፕሎማቶቹ በኩል መላኩን የአውሮፓ ኅብረት አመልክቷል።


የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮች ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመቐለ ተወያይተዋል፡፡ ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ወደ መቐለ ሄደው ከህወሓት አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ለፌደራል መንግሥቱ የሚሰጥ ደብዳቤ ከክልሉ ሬዚዳንት መቀበላቸው ተመልክቷል፡ ኅብረቱ እንዳለው ቀደም ሲል ከፌደራል መንግሥት ጋር በተደረጉ ውይይቶች የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ስምምነት እንዳለ
ገልጸዋል።


የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ የተቋረጡት መሠረታዊ አግልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር ዋነኛው እንቅፋት ለጥገና የሚሰማሩ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው በማለት ሲገልጽ ቆይቷል። ወደ መቐለ አቅንቶ በነበረው የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ የጋራ ዲፕሎማሲያዊ ቡድን በኩል ከትግራይ አመራሮች በኩል የተሰጠው ዋስትና አገልግሎቶቹ በአስቸኳይ መልሰው እንዲጀመሩ በር ይከፍታል ተብሏል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *