loading
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ የቅርብ ተመልካች ሆና እንደማትቀጥል አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ የቅርብ ተመልካች ሆና እንደማትቀጥል አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ በቀጠናው የወደብ አማራጮችን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ደመቀ ይህን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡


በማብራሪያቸው ወቅትም ይህ ትልቅ ሀገርና ህዝብ የወደብ አማራጭ እንዲኖረው ለማስቻል በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር የጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂ ቀርጸን እየሰራን ነው ብለዋል። በኬኒያ፣ በሶማሌላንድና በኤርትራ በመተማመን ላይ የተመሰረተ የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ካለት ቅርበት አንጻር በቀጠናው ተጠቃሚ እንጂ የቅርብ ተመልካች ሆና የምትቀጥልበት አግባብ እንደማይኖር ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት።


በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያን ያላሳተፈ አደረጃጀት ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ኢትዮጵያ በትብብር፣ በፍትሃዊነትና በሚዛናዊነት በቀጠናው ያላትን ጥቅም ማስከበርን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጋ መስራቷን ትቀጥላለች  ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ከወራት በኋላ ሃይል
ማስተላለፍ ሊጀምር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተዘረጋ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር በሐምሌ ወር መጨረሻ ሃይል ማስተላለፍ እንዲጀምር ስምምነት ላይ መደረሱን ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *