loading
የሕወሓት ቡድን በአማራ ክልል ከተሞች አሰቃቂ ግፍና ወንጀሎችን መፈፀሙን አመንስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ፡፡

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 የሕወሓት ቡድን በአማራ ክልል ከተሞች አሰቃቂ ግፍና ወንጀሎችን መፈፀሙን አመንስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ፡፡
ተቋሙ ዛሬ ባወጣው ሪፖርቱ የቡድኑ አባላት በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሆን ብለው በርካታ ንጹሃንን መግደላቸውን፣ ሴቶችን በቡድን መድፈራቸውን እንዲሁም ከፍተኛ የግልና የመንግስትን ሃብት መዝረፋቸውን ተናግሯል፡፡


በተለይ ቆቦ እና ጭና በተባሉ ሁለት አካባቢዎች በነሃሴ መጨረሻና መስከረም መባቻ ላይ በንጹሃን ላይ አረመኔያዊ ተግባር መፈፀማቸውን ነው አመንስቲ የገለጸው፡፡
ለአብነትም በቆቦና አካባቢው ወረራ ሲፈጽሙ የመቃወም አዝማሚያ በሳዩት ሰዎች ላይ ያለርህራሄ ድብደባና ግድያ እንደፈጸሙ ተቋሙ የአይን እማኞችን አነጋግሬ ደረስኩበት ባለው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡


ይህም የሕወሓት ቡድን ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ሊከተሏቸው የሚገቡትን ዓለም አቀፍ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ህግጋትን በአደባባይ መጣሱን የሚያሳይ ነው ብሏል ሪፖርቱ፡፡ ተቋሙ አያይዞም የሕወሓት አመራሮች ይህን በምርመራ የተረጋገጠ ግፍ በአስቸኳይ እንዲያቆምና የዚህ አይነት ድርጊት የፈጸሙ አባላቱን ከሰው ሃይሉ ማስወገድ አለበት ሲል አሳስቧል፡፡


ቡድኑ በአጠቃላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ተግባራትን መፈጸሙን የገለጸው አመንስቲ ኢንተርናሽናል ከፈጸማቸው አፀያፊ ድርጊቶች መካከል ዘርን መሰረት ያደረጉ ዛቻና ስድቦች ይገኙባቸዋል ብሏል፡፡ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካና ታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የተፈጸመውን ወንጀል በመመርመር አጥፊዎች እንዲጠየቁና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች መብቶቻቸው እንዲከበሩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *