loading
በሱዳን በኩል ወደ ሀገር ሊገባ ሲል የተደመሰሰው የህወሃት ቡድን

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6 ፣ 2013 ከሱዳን በመነሳት በማይካድራ አድርገው ወደ ሀገር ሊገቡ የነበሩ 320 የህወሃት ሀይል አባላት ተደመሰሱ፡፡ የህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ ሀላፊ ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንዳሉት ይህ ቡድን በማይካድራ ጭፍጨፋ አድርሶ ወደ ሱዳን ሸሽቶ የነበረ ነው፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ በሰጡት መግለጫ ቡድኑ ዳግም ተደራጅቶ የተለያዩ የመገናኛ መሳሪያዎችንና መድሀኒቶችን በመያዝ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ሙከራ ሲያደረግ በመገኘቱ ተደምስሷል ብለዋል። ሀላፊው አክለውም ሀገራዊ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው በአሜሪካ ይገኙ የነበሩና ሀገርን በመካድ ሱዳን ካርቱም ከሚገኙ የቡድኑ አመራሮች ጋር ወደ ሀገር ውስጥ የመገናኛ መሳሪያዎችና መድሀኒቶችን ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ በሰራዊታችን ተደምስሰዋል ብለዋል።

በሱዳን መንገድ ላይ በውሀ ጥም የተንጠባጠቡ አባላቶቹና እጃቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑትም ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል ። ብዛት ያለው የሬድዮ መገናኛ ፣ ሳተላይት ስልኮችና መድሀኒትም በቁጥጥር ስር መዋሉን ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል። መረጃውን ያገኘነው ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ነው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *