በሰሜን አሜሪካ በአዉሮፓ በአዉስትራሊያ እና በአፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያን የሚያፈርሱ አካሄዶችን እንደሚቃወሙ ገለጹ፡፡
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2013 በሰሜን አሜሪካ በአዉሮፓ በአዉስትራሊያ እና በአፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያን የሚያፈርሱ አካሄዶችን እንደሚቃወሙ ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያዉያን ዲያስፖራዎች ወቅታዊ የሀገራቸዉን ሁኔታ በተመለከተ ባወጡት የጋራ መግለጫ ፤ አደገኛ የዉስጥ ግጭት እና የዉጭ ከበባና ዛቻ ባለበት በዚህ የታሪክ ወቅት ልዩነታችን ላይ እያተኮርን የምንበታተንብት ጊዜ ሳይሆን፤ የተነሳብንን አደጋ በጥልቀትና አርቆ በማሰብ መርምረን በምን መልኩ እንመክታለን በሚለዉ ላይ ተቻችለን መተባበር አለብን ብለዋል፡፡
ዘረኛ ጽንፈኞች ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸዉን እያሳደዱ መግደላቸዉን በደስታ የሚደግፉ ጠላቶች አሉን ያሉት ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያኑ ፤በእጅ አዙር ጽንፈኞችን እየደገፉ እርስ በእርስ እንድንባላ አድርገዉ የሀገራችንን መበታተን አድፍጠዉ እየጠበቁ መሆኑን አወቀን ልንተባበር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሁን ያለዉ መንግስት በችግር የተዘፈቀች ኢትዮጵያን እንደተቀበለ ቢታወቅም ለተከሰተዉ እልቂት ግን ከተጠያቂነት አያድነዉም ያለዉ መግለጫዉ ፤ በሀገራችን በግፍ ንጹሃንን እንዲገደሉ እንዲፈናቀሉና ጉዳት እንዲደርስባቸዉ ያደረጉ አካላትም ለህግ እንደሚቀርቡ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን የተጋረጠብንን አደጋ ለመቋቋምና ሀገራችንን ከመበታተን ለማዳን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረዉ መንግስት በመሆኑ እየተቸነዉ አስከነ ድክመቱም ቢሆን ከመንግስት ጎን ቆመን ሀገራችንን ጭራሽ ከመፍረስ ልንታደጋት ይገባል ብለዋል፡፡ በመግለጫቸዉም ፤ ሀገራዊ ምረጫ በግዜዉ እንዲካሄድ፤ ንጹሀንን በግፍ የገደሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ እና የሀገራችን ሉአላዊነትና ፖለቲካዊ ነጻነት በፍጹም ለድርድር እንዳይቀርብ በጋራ መቆም አለብን የሚል ጥሪ ለኢትዮጵያዉያን አስተላልፈዋል፡፡