loading
ለትግራይ ወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ የድጎማ በጀት የሚተላለፍበት አሰራር ዝግጅት ማጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 ለትግራይ ወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ የድጎማ በጀት የሚተላለፍበት አሰራር ዝግጅት ማጠናቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደተናገሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ሚኒስቴሩ ለክልሉ ወረዳዎች ፣ ከተሞችና ቀበሌዎች የድጎማ በጀቱን የሚያስተላልፍበትን የአሰራር ዝግጅት አጠናቋል፡፡በሚኒስቴሩ የተዘጋጀው የበጀት ድጎማ አሰራር በሚቀጥለው ሳምንት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በጀቱ በወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ አስተዳደር አካላት የባንክ ሂሳብ በኩል እንደሚተላለፍ አስታውቀዋል፡፡የአስተዳደር አካላቱ የባንክ ሂሳብ ማስተላለፊያ ደብተር ካላቸው በዚያው በኩል ከሌላቸው ደግሞ አዲስ የባንክ ሂሳብ በመክፈት በጀቱ እንዲደርሳቸው እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች ህዝቦች የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የምግብ ዋስትና እና ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ድጋፍ እንዲያገኘ ይደረጋል ብለዋል፡፡የፌዴሬሽን ምክር መስከረም 26 ስብሰባ አድርጎ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የፌደራል መንግሥት “የወረዳ፣ የከተማና የቀበሌ አስተዳደሮችን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ የሥራ ግንኙነት ማድረግ አለበት።” የሚል ውሳኔ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *