ከወደቀው አውሮፕላን ውስጥ በቁፋሮ የተገኘው ብላክ ቦክስ ለመርማሪዎች ተሰጠ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ከሆነውና ትናንት ቢሾፍቱ አቅራቢያ ከወደቀው ቦይንግ 737 ዳሽ ማክስ ኤይት አውሮፕላን ስብርባሪ ውስጥ የተገኘው የመረጃ መዝጋቢ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ምርመራውን ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች መሰጠቱ ታወቀ።
የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለው ሁነኛውን ጠቅሶ እንደዘገበው የመረጃ ሳጥን ርክክቡ ተካሂዷል።
የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ ወሳኝ መሳሪያ ነው የተባለው ይኸው የመረጃ ሳጥን በዚህ ፍጥነት ሊገኝ መቻሉ በአደጋው ምክንያት ዙሪያ የሚሰነዘሩ መላ ምታዊ መረጃዎችን በማስቀረት ሳይንሳዊ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
ለአርትስ አስተያየታቸውን የሰጡ የአቪዬሸን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የመረጃ ሳጥኑ የአደጋ ምርመራ በማካሄድ ላይ ለሚገኘውና ከተለያዩ ሃገራት ለተውጣጣው የመርማሪዎች ቡድን የምስራች ነው።
ብላክ ቦክስ ወይም ጥቁር ሳጥን ተብሎ የሚጠራው የመረጃ ሳጥን የአውሮፕላን ሞተር ከተነሳ በኋላ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የሚመዘግብ መሳሪያ ነው ።
ይህ መሳሪያ አንድ አውሮፕላን የመከስከስም ይሁን አየር ላይ የመፈንዳት ወይም በባህር ውስጥ የመስጠም አደጋ ቢደርስበት የትኛውንም አይነት አደጋ ተቋቁሞ መትረፍ የሚችል ሲሆን በከፍተኛ ቃጠሎ ውስጥ እንኳን ሆኖ በ2 ሺህ ፋራናይት የሙቀት መጠን ለ 1 ሰዓት ያክል ሳይቃጥል ወይም ሳይጎዳው መቆየት እንደሚችል ይነገራል።
መሳሪያው የሚይዘው መረጃ መጠን እስከ 3400 ጊጋ ይደርሳል። በሌላ አነጋገር አንድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ሳኦ ፖሎ ብራዚል ደርሶ እስኪመለስ ድረስ ያለውን
የአብራሪውን እንቅስቃሴ፣ የአውሮፕላኑን ፍጥነት፣ ከፍታውን፣ የነዳጅ ሁኔታና ሌሎችም ሁሉ እንቅስቃሴ መዝግቦ ማስቀመጥ ይችላል።
ከፍተኛ እርጥበት የመቋቋም አቅም ያለው ይኸው መሳሪያ በውሃ ውስጥ ሆኖ እንኳን የያዘውን መረጃ ሳያጣ ለ2 ዓመት መቆየት እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በውሃው ውስጥ 20 ሺህ ጫማ ሰጥሞ እንኳን ለ30 ሰአት ለመረጃ ፈላጊዎች መረጃ ለማቀበል በሚያስችለው ብቃት የተሰራ ነው።
በዚህ የተነሳም ማናቸውም የአውሮፕላን አደጋ ባጋጠመ ጊዜ የአደጋ መርማሪዎችና ፍለጋ የሚያካሂዱ ባለሙያዎች በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን ከማዳን እና የሞቱትን አስከሬን ከማግኘት ጎን ለጎን ቀዳሚ እና ትልቁ ስራቸው ይህንን ጥቁር ሳጥን ማግኘት ነው።