ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
ሰባት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግንባር ለመስራት የሚያስችላቸውን ጥምረት ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
ሰነዱን የተፈራረሙት የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የአፋር ህዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ህዝቦች ነፃነት ፓርቲ እና የኦሮሞ ህዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ናቸው።
ፓርቲዎቹ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት ግንባሩ በሃገሪቱ ያለውን የመድብለ ፓርቲ ጅምር ስራዎችን በማጠናከር በሃገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማጠፍ የሚሞክሩ አካላትን ለመመከት ያግዛል ብለዋል ።
ከዚህ ባለፈም ገንባሩ በሃገሪቱ በህግ አግባብ ብቻ የሚዳኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ማገዝና የበኩሉን ድርሻ መወጣት አላማው መሆኑም ተነስቷል።
የዜጎች መብት እንዳይጣስ መስራትና በሃገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን ግንባሩ እንደሚሰራም ነው የተገለጸው።
ግንባሩ ከሁሉም ፓርቲዎች የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ወደ ስራ ይገባል ተብሏል።
ኮሚቴው ከእያንዳንዱ ፓርቲ የተውጣጡ ሶስት ሶስት አባላት ሲኖሩት፥ ጥምረቱ በምርጫ ቦርድ በህጋዊነት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ተገልጿል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።