ቶተንሃም እና ማድሪድ የቻምፒዮንስ ሊግ ድል አግኝተዋል
ቶተንሃም እና ማድሪድ የቻምፒዮንስ ሊግ ድል አግኝተዋል
ትናንት ምሽት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡
የጀርመኑን ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ያስተናገደው ቶተንሃም 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል፡፡
በቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ከመረብ ያላገናኙ ቢሆንም ስፐርሶች ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ግብ ማስቆጠር ጀመሩ፡፡
ደቡብ ኮሪያዊው ሰን ሁንግ ሚን በ47ኛው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ፤ ሰን ላስቆጠራት ጎል ምክንያት የሆነው ያን ቬርቶገን ሁለተኛዋን እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ፈርናንዶ ዮሬንቴ የማሳረጊያዋን ሶስተኛ ግብ፤ ከመረብ በማገናኘት የማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ቡድን ለመልሱ የሲግናል ኤዱና ፓርክ ግጥሚያ ጠቃሚ የሆነ ስንቅ ይዟል፡፡
ሌላኛው ግጥሚያ ሆላንድ ምድር ላይ የተካሄደ ሲሆን ሪያል ማድሪድ በዩአን ክራይፍ አሬና አያክስን 2 ለ 1 በመርታት ሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ የሚከናወነውን የመልስ ጨዋታ እንዲቀለ አድርጎታል፡፡
ከወጣቱ ቪኒሽዬስ ጁኒዬር የተሻገረችውን ኳስ ካሪም ቤንዜማ በ60ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ማድሪድ መሪ ቢሆንም፤ ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ሃኪም ዛይች ከመረብ ያገናኛት ጎል ባለሜዳዎችን አቻ አደረገች፤ ነገር ግን ዳኒ ካርቫሃል መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ከመጠናቀቁ ሶስት ደቂቃዎች አስቀድሞ ለማድሪድ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡
የቪዲዮ አሲስታንት ሪፈሪ (ቫር) በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረ ሲሆን የአያክሱ ኒኮላስ ታግሊያፊኮ ያስቆጠራት ግብ በቫር እገዛ ተሽራለች፡፡
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በ16ቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ እና ዕረቡ ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡