loading
ለስድስት ወራት በቆየው የምህረት አዋጅ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ

ለስድስት ወራት በቆየው የምህረት አዋጅ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ።

ሀምሌ 13 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ የገባው የምህረት አዋጅ ከትናንት በስቲያ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ተጠናቅቋል።

የምህረት አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በቆየባቸው የስድስት ወራት ጊዜያትም ከ13 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ዕለት ድረስ የወንጀል ክሳቸው በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተይዞ የነበሩት እነዚሁ ግለሰቦች የምህረት ሰርተፊኬት መውሰዳቸውንም ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

አዋጁ ስራ ላይ የዋለው ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት በተፈፀሙ ወንጀሎች ይመለከታቸዋል ለተባሉ ግለሰቦች ምህረት ለማድረግ እንደነበር ዐቃቢ ሀግ አስታውሷል።

በዚህም መሰረት ክትትል የሚደረግባቸው፣ ምርመራ የተጀመረባቸው እና ውሳኔ አግኝተው በየማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ግለሰቦች የአዋጁ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከምህረት አዋጁ ተጠቃሚዎች ውስጥም አብዛኞቹ በአካል በመቅረብ የምህረት ሰርተፊኬት የወሰዱ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ደግሞ በተወካይ እና በድረ-ገፅ አማካኝነት ፎርም ሞልተው መውሰዳቸው ተገልጿል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *