በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውር የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውር የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው በክልሉ በኑዌር ብሄረሰብ ዞን በተደረገበት ክትትል ሲሆን ሃያ ስድስት ክላሽ፣ አንድ ብሬንና ሃያ የጥይት ካዝና ተገኝቶበታል ሲል የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሳይመን ቲያች እንዳሉት የጦር መሳሪያውን ይዞ የተገኘው ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምርመራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ውጤቱ ለፍርድ ቤት እንደሚላክም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
የጦር መሳሪያዎቹና ተጠርጣሪ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በህብረተሰቡ ጥቆማና ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ የክትትልና የቁጥጥር ስራ መሆኑን አቶ ሳይመን ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ አካላት የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ የጋምቤላ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር ከሚጋራው ሰፊ የድንበር ወሰን ጋር ተያይዞ ያለ በመሆኑ፤ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡