ሃገር በቀል ዕውቀቶች በምርምር አልፈውና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ወደ ህብረተሰቡ ለማውረድ የሚያስችል መመርያ ፀደቀ
ሃገር በቀል እውቀቶች በምርምር አልፈውና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ወደ ህብረተሰቡ ለማውረድ የሚያስችል መመርያ ማፅደቁን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር መስተማር ስራዎቻቸው በተጨማሪ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ እና ከዛም አልፎ ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ግኝቶችን በምርምር ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎችም በተወሰነ ደረጃ ይህን አብይ ጉዳይ ለማሟላት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ዪኒቨርስቲዎች ሀገር በቀል እውቀቶችን መነሻ አድርጎ መስራት ላይ በርካታ ውስንነቶች የሚስተዋሉባቸው መሆኑ ነው የተገለፀው።
የወሎ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መንገሻ አየነ ተመራማሪዎች መነሻቸውን አጠገባቸው ያለውን ዕውቀት ከማድረግ ይልቅ በውጪ ዕውቀቶች ላይ የማተኮር እና እነዛን ገልብጦ የማምጣት አዝማሚያ እንደሚታይባቸው ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር የቻለ ከበደም የአቶ መንገሻ አየነ ሃሳብ ይጋራሉ።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ የሚጠቀምባቸውን የግብርና ዘዴዎች በተወሰነ ደረጃ ለማሻሻል እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች መስራቱን ዶክተር የቻለ ተናግረዋል።
በቀጣይ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ስራዎች መኖራቸውን የገለፁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ከሚጠበቅበት አንጻር የተሰራው እና በሂደት ላይ ያለው ስራ በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፥ የከፍተኛ ትምህር ተቋማት የምርምር መነሻቸው አካባቢያቸውን ማየት እና ወደ ህብረተሰቡ ገብቶ መፈተሽ የሚገባቸው ቢሆንም አብዛኞቻቸው ግን ይህንን ሲያደርጉ አይስተዋልም ብለዋል።
በዚህ ምክንያትም በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ባሉበት አከባቢ ብቻ ተቀብረው እንዲቀሩ ማድረጉን ነው የገለጹት።
ችግሩን ለመፍታትም ተመራማሪዎች ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ባህላዊውን እውቀት መጠቀም እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ይህን አይነት አሰራር እንዲለመድ እና እንዲተገበር ለማድረግ ከዛም አልፎ በፊት ዩኒቨርሲቲዎች ሰጪ ማህበረሰቡ ተቀባይ የነበረውን አሰራር ወደ ዕውቀት መመጋጋብ እና አብሮ መስራት እንዲቀየር ለማድረግ መመርያ ወጥቶ መፅደቁ ነው የተገለፀው።
መመርያው በአሁኑ ወቅት ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች መሰራጨቱን የገለፁት ሚንስትር ዴኤታው ሀገሪቱ ያሏትን ሀገር በቀል ዕውቀቶች በምርምርና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።