ቴሬዛ ሜይ ዳግም ህዝበ ውሳኔ የማይታሰብ ነው አሉ
አርትስ 08/04/2011
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለመለያየት የጀመረችው አሰልቺ ጉዞ መቋጫ ባላገኘበት በአሁኑ ወቅት ዳግም ህዝበ ውሳኔ ይካሄድ የሚል ግፊት በዝቶባቸዋል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው የእንግሊዝ ህዝብ የሚበጀውን እንዲመርጥ እድል ሊሰጠው ይገባል ከሚሉት ሰዎች መካከል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል፡፡
ቶኒ ብሌር በሰጡት አስተያየት ከ30 ወራት በላይ የፈጀው ድርድር በሀገሪቱ ቀውስ ከመፍጠር ያለፈ መፍትሄ ሲያመጣ አላየንም ስለዚህ ሌላ አማራጭ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሜይ በበኩላቸው ብሌር ይህን ሲናገሩ የነበሩበትን ቢሮ እየሰደቡ መሆኑን ማወቅ እንዴት ተሳናቸው በማለት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ወርፈዋል፡፡
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣር ከ1990 አስከ 1997 እንግዝን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ጆን ሜጀርም የቶኒ ብሌርን ሀሳብ ደግፈው፤ ቴሬዛ ሜይ ለዳግም ምርጫው እንዲዘጋጁ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ግን ዳግም ህዝበ ውሳኔ ማድረግ የእንግሊዝን ህዝብ መናቅና እንደ መንግስት የገባነውን ቃል እንደማጠፍ ይቆጠራል የሚል ፅኑ አቋም አላቸው፡፡
አሁን ላይ የእንግሊዝ ፓርላማ በተከፋፈለ ሀሳብ በጉዳዩ ዙሪያ እየተከራከረበት ነው፡፡ ምርጫው ይካሄድ የሚሉት ወገኖች የአሁኑ ምርጫ ከቀድሞው የሚለየው ብሪ ኤግዚት ማለት ምን እንደሆነ ህዝቡ ገብቶታል ይላሉ፡፡
በሌላኛው ወገን ህዝበ ውሳኔው ዳግም አይካሄድ የሚሉት ደግሞ መንግስት የገባውን ቃል ካላከበረ በህዝቡ ዘንድ ያለው መታመን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡