ፈረንሳይ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ እየተዝናኑ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ የከፈተውን ግለሰብ እያሰሰች ነው
ፈረንሳይ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ እየተዝናኑ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ የከፈተውን ግለሰብ እያሰሰች ነው
አርትስ 04/04/2011
ግለሰቡ በምስራቃዊ ፈረንሳይ ከተማ ስትራስበርግ የአውሮፓውያንን ገና በዓል ምክንያት በማድረግ እየተዝናኑ የነበሩ ሰዎች ላይ ‘አላሁ አክበር ‘ ብሎ ተኩስ በመክፈት ሁለት ሰዎችን ገድሎ አስራ አንድ ሰዎችን አቁስሏል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ቸሪፍ ቺካት የተባለው ይህ ግለሰብ እስር ቤት በነበረበት ወቅት አክራሪ እንደሆነ ይነገር ነበር፤ ፈረንሳይም ግለሰቡን ለመያዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰማርታለች።
የፓሪስ ከተማ አቃቤ ህግ ሪሚ ሄትዝ እንደገለፁት ግለሰቡ የ29 ዓመት ወጣት ሲሆን ጥቃቱን የፈፀመበት ቦታ ላይ መሳሪያና ስለት ይዞ እንደነበር እና ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ በታክሲ ከአካባቢው ተሰውሯል ብለዋል።
ጥቃቱ በተፈፀመ ምሽት ከግለሰቡ ጋር ግንኙት እንዳላቸው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ሃይሎችን አሰማርተው ፍለጋውን እያካሄዱ ቢሆንም ግለሰቡ ግን ከፈረንሳይ ሳይወጣ እንዳልቀረ እየተጠረጠረ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ክሪስቶፍ ካስታነር በበኩላቸው የገና በዓል ዝግጅቶች በሚካሄድባቸው ቦታዎች እንዲሁም ድንበሮች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ ነዉ ብለዋል፡፡
የስትራስበርግ ከተማ ከንቲባ ሮናልድ ሪስ በገና በዓል የገበያ ስፍራዎች ዝግ እንደሚሆኑና በከተማዋ የስብሰባ ማዕከሎችም ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ብለዋል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፡፡