የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከመቶ ሚሊዮን አለፈ
የመንግስታቱ ድርጅት የስነ-ህዝብ ፈንድ በዘንድሮው የዓለምን ህዝብ ቁጥር እድገት የተመለከተ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ107 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት የዓለም ህዝብ ብዛት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ደርሷል። ከዚህ ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖረው በአፍሪካ ነው።
በዓመታዊ የእድገት ምጣኔ በተካሄደ ስሌት በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ107 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን በሃገሪቱ ያለው የወሊድ ምጣኔ በከተማ 2 ነጥብ 3፣ በገጠር ደግሞ 5 ነጥብ 2 መሆኑን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የስነ-ህዝብ ፕሮግራሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሆርዶፋ እንዳሉት ዛሬ ባላደጉት የአለም አገራት ከ214 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ሴቶች ላልተፈለገ እርግዝና ይዳረጋሉ።
ይህ የሚሆንበት ምክንያትም በማህበረሰቡ ዘንድ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት የማግኘትና በአግባቡ የመጠቀም እድሉም ሆነ ግንዛቤው አናሳ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የህዝብ ቁጥር እድገትን ተከትሎ የሚገጥመውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የቤተሰብ ምጣኔን ማስፋፋት እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በፆታዊ ጥቃት፣ በአስግድዶ መድፈርና ያለ እድሜ ጋብቻ ላይም ጠንከር ያሉ ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ የተቋሙን ሪፖርት ተንተርሰው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።