loading
ስምምነት ከተደረገባቸው አገራት ውጪ የሚደረግ ሕገወጥ ጉዞ መቆም እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ

ከኢትዮጵያ ጋ ስምምነት ከፈጸሙ ሶስቱ የአረብ ሀገራት ውጪ የሚደረግ ህገወጥ ጉዞን  በማስቆም ባለድርሻ ኣካላት የበኩላቸውን  እንዲወጡ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል፡፡

ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያውን የሰጡት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከል ኃላፊነት ለተሰጣቸው የፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ፣ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው መልዕክቱን ያስተላለፉት ፡፡

አቶ ደመቀ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን መብታቸው ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታ ሰርተው ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ከሳዑዲ አረቢያ፣ኳታር እና ጆርዳን ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል።

በዚህ መሰረትም ሰራተኞችን ለመላክ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ ከኢትዮጵያ ጋ ስምምነት ወዳልፈረሙት እንደ ኩዌት፣ባህሬን፣የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ቤይሩት እና ኦማን በቱሪስት፣ በዘመድ ጥየቃ፣ በንግድና የመሳሰሉ ቪዛዎች ከሀገር እየወጡ ሕገወጥ የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ግለሰቦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዚህ መልኩ ዜጎችን ወደ ውጭ የሚልኩ ኤጀንሲዎች እንዳሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ተቋማቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት ለመታደግ የሁለትዮሽ ስምምነት ወዳልተደረገባቸው ሀገራት ለሥራ የሚሄዱ ዜጎችን እንዲያስቆሙና  በዚህ ሁኔታ ዜጎችን በሚልኩ ኤጀንሲዎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *