loading
ህገወጥ አፍሪካውያን ስደተኞች ወደአውሮፓ እንዳይገቡ ህብረቱ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር መከረ

የአውሮፓ ህብረት ወደአውሮፓ ሃገራት የሚገቡ ህገ ወጥ አፍሪካውያን ስደተኞችን ለማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሰሜን አፍሪካ ሃገራት ጋር መክሯል።

በምክክሩ ወቅት ሃገራቱ ለውይይት ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል አፍሪካውያን ዜጎች ለምን ምግብና መጠጥ እንዲሁም መጠለያ ፍለጋ ወደ ሩቅ ምስራቅና የአውሮፓ ሃገራት እንደሚሰደዱ መለየትን ያካትታል፡፡

ህብረቱና ሃገራቱ ደረስንበት ባሉት መረጃ መሰረትም ወደብ ላይ ህገወጥ ስደትን አባባሽ ደላሎች እንዳሉና እነዚህን ህገ ወጥ ደላሎች ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረትና ቱርክ እያሳደሩ ባሉት ተፅዕኖ የስደተኛ ቁጥር እየቀነሰ ቢመስልም በ2015 በዋናነት ከሶሪያና ከኢራቅ እርስበእርስ ጦርነት ምክኒያት ከ1ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሃገራት መፍለሳቸው ተነግሯል፡፡

ህገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ 95 በመቶ እንደቀነሰ ቢነገርም 28 የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ተመሳሳይ አቋም ባለመያዛቸው የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለም በምምክሩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

ከወደ ሜዲትሪኒያን አቅጣጫ የሚገኙት እንደነ ግሪክ፤ጣልያን እና ስፔን ለብቻቸው ህገወጥ ድርጊቱን ለማስቆም እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸው ቢታወቅም ውጤታማነታቸው አጠራጣሪ ነው እንደ ሃገራቱ አባባል፡፡

ሃገራት ስደትን ከፖለቲካዊ ጥቅምና ከሃገር ልዕልና ጋር አያይዘው መከራከራቸው ባይጠላም ስለ ሰው ልጅ ህይወት እያወራን እንደሆነ ግን መዘንጋት የለበትም ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ይህንን ተግባር ግን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል አይጠበቅብንም ብለዋል። ዜናው የአሶሼትድ ፕሬስ ነው።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *