የአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተመረቀ
አርትስ 27/01/2011
በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመንግስት ለመገንባት ከታቀዱት የኢንዱስትሪ ፖርኮች 2ኛው የሆነው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፖርክና ሌሎቹም ኢንቨስተሮችን በመሳብማነቆዎቻቸውን በመፍታት በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት ፣የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ምርታማ መሆን እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑ ታምኖበት በ1ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን በመንግስት የቦሌ ለሚ፣በግል ደግሞ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወሳል::
እነዚህን እና በአለም ላይ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ እና ለካቢኔ ቀርቦ የኢንዱስትሪ ፖርኮችን በተሻለ ለማልማት የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል::
ከዚህ ማሻሻያ በኋላ በቅድሚያ የሃዋሳ ፣ ቀጥሎም የኮምቦልቻና የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠናቀው የተመረቁ ሲሆን ፤ በዛሬው ዕለት በ2ኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ለመገንባት ከታቀዱት 4ኛው የሆነው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው ዕለት ተመርቋል::
በመንግስት ከተገነቡት የፓርኩ 19 ፋብሪካዎች እና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ህንጻዎችና ሌሎች ፋሲሊቲዎች በተጨማሪ በፓርኩ ውስጥ ጃንሱ-ሰንሻይን እና ኪንግደም የተባሉ ሁለት ግዙፍ የግል ፉብሪካዎች በግንባታ ላይ ሲሆኑ ፤ ጃንሱ-ሰን ሻይን በ80 ሄክታር እንዲሁም ኪንግደም በ30 ሄክታር ላይ የሚያርፉ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ናቸው::
ፓርኩ በተሟላ ሁኔታ የማምረት ደርጃ ላይ ሲደርስ ከ1ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የኤክስፖርት ገቢ እና በ2 ሽፍት ከ60ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል::