የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ነው አለ፡፡
ተቋሙ ባለፉት አመታት ለፓርቲ የወገነ አሰራር መተግበሩና ከተሰጠው አገራዊ ተልእኮ ውጪ ዜጎችን የማፈን የማሰርና ኢሰብአዊ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱ ተቋሙ እንዲፈራ አድርጎት ቆይቷል ተብሏል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል አደም መሀመድ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ከተቋሙ አሰራር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ተቋሙ የተቋቋመበትን አዋጅ ማሻሻልን ጨምሮ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ነው ፡፡
በተቋማዊ የሪፎርም ስራው በቀጣይ ተቋሙ በህዝብ አመኔታን ያተረፈ ከመሆን ባለፈ ህዝባዊና አገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል፡፡
ይህን ለማሳካትም የተቋሙ ሰራተኞች ከምንም አይነት የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ሙያዊ ሀላፊነታቸውን የሚያስቀድሙና በአገሪቱ የሚለዋወጡ መንግስታትን የሚያገለግሉ እንዲሆኑ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡