loading

በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ የህግ ታራሚዎች ተመረቁ

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሸዋሮቢት ተሀድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት በልዩልዩ መሰረታዊ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለተከታታይ 6 ወራት ከይፋት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጂ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን የህግ ታራሚ ተማሪዎች ቅዳሜ በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት አዳራሽ አስመርቋል፡፡

ስልጠናው ከወርሓ መስከረም 2011ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን 370 ሰልጣኞች ሰልጥነው የተሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና ወስደው ያለፉ 235 የህግ ታራሚ ተማሪዎች ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሸዋ ሮቢት ተሀድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ኮማንደር እንዳሻው ማሙዬ እንደተናገሩት “የመንግስትን የለውጥ ጉዞ ማዕከል በማድረግ ማረሚያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የህግ ታራሚዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ሙያዎች ላይ አሰልጥኖ በማስመረቅ ፍርዳቸውን ጨርሰው ሲወጡ እራሳቸውን ፣ ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል ማመቻቸትና በክህሎት በቅተው እንዲወጡ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ኮማንደሩ አያይዘውም ተመራቂ ታራሚዎችን ልዩ የሚያደርጋቸው በውጭና በውስጥ ያሉ ለግጭት የሚዳርጉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው እጃቸውን ላልተፈለገ ሁከትና ብጥብጥ ሳይሰጡ ከአላማቸው ግብ ላይ መድረሳቸው ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም በማረሚያ ቤቱ ስም ለታራሚዎች ላሳዩት መልካም ስነ-ምግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ማረሚያ ቤቱ በ9 የተለያዩ ሞያዎች ያሰለጠነ ሲሆን የሙያ መስኮቹም፡- የልብስ ስፌት ሙያ፣ የእንጨት ስራ፣ከ የብርታ ብርት ስራ፣ የሽመና ሙያ ስራ፣ የኤሌትሪክ ስራ፣የቧንቧ ጥገና የውበት ሳሎን ስራ፣ የህንፃ ግንባታ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራ ሙያ ናቸዉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *