loading
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ጋር ተወያዩ

አርትስ 30/02/2011
ውይይቱ በአካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄ እንዲሁም የክልል አስተዳደር ወሰኖች ላይ ያተኮረ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ፣ የቅማንት ማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ምላሽና አተገባበሩ፤ እንዲሁም አማራ ክልል ከትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ባለው የወሰን አከላለል ሁኔታዎች ላይ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፥ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርን በተመለከተ መንግስት፣ የታሪክ ሰነዶች፣ የታሪክ አጥኚዎች እና ከዚህ በፊት የነበሩ ስምምነቶችን የማጥናትና የመመርመር ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ጉዳዩ ብዙ ዘመን ሲንከባለል የኖረ መሆኑን በማንሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ቢያስቸግርም፤ ሁለቱን ሀገራት በሚያስማማ እና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አማራ ክልልን ከሚያዋስኑት የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ትግራይ ክልሎች ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰንና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በብዙ ክልሎች የሚነሳ ሀገር አቀፍ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያና ሶማሌ፣ በደቡብና ኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች መካከልም የወሰን አከላለል ጥያቄ እየተነሳና ምላሽም እየጠበቀ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፥ ለሀገር አቀፍ ችግር መፍትሄው ሀገር አቀፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ይህንንም ለማድረግም በሀገሪቱ እየተሰራበት ያለውን የክልሎች የአስተዳደር ወሰን አከላለል ጥቅምና ጉዳቱን የሚያጠና መፍትሄም የሚያስቀምጥ ኮሚሽን እየተቋቋመ መሆኑን ገለፀዋል።
ኮሚሽኑ ምህራን፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ የተፎካካሪ ፓለቲከ ፓርቲዎችና ሌሎች ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት የተካተቱበት ነው።
ይህ ኮሚሽንም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመልክተዋል።
የቅማንት ማንነትና የራስ አስተዳደርን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ የአማራ ክልል ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢና ትክክል ነው ብለዋል።
በውሳኔው መሰረት የራስ አስተዳደር እንዲመሰርቱ የተፈቀደላቸው 69 ቀበሌዎች የራስ አስተዳደር መዋቅር ስራው እንዲከናወን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
እልባት ያላገኙ ተጨማሪ ሶስት ቀበሌዎች ጉዳይንም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚላክ ገለልተኛ ቡድን ወደ አካባቢው ወርዶ በማጥናት በቅርቡ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።
በቅርቡ በምዕራብ ጎንደር ዞንና አካባቢው የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈጠረው መፈናቀልና ሞት ከዚህ በኋላ መደገም የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎች በውይይትና በሰከነ መንፈስ ብቻ ሊቀርቡና ሊመለሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *