loading
ግንቦት ሃያን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ግንቦት ሃያን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ግንቦት 20 ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈችባቸውን አበይት የታሪክ ምዕራፎች ስናስብ ከምናስታውሳቸው ዕለታት ውስጥ አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ዕለት የኢትዮጵያን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መልክአ ምድር የቀየረ ታሪካዊ ዕለትም መሆኑንም አስታዉሰዋል፡፡

ይህን በዓል ዛሬ ካለችውና ለወደፊቱም እንገነባታለን ብለን ከምናስባት ኢትዮጵያ አንጻር ማክበር የተሻለ ብቻም ሳይሆን ለሁላችንም የሚበጅ ነውያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የወደፊቷን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ አንድ መሠረታዊ ነገር ላይ ተማምነን መነሣት አለብንም ብለዋል፡፡

በሀገራችን ‹እኔም አለኝ ቁስል፣ ያንተን የሚመስል› የሚል ትልቅ አባባል አለ፡፡

ይህ አባባል ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ሁለት ሐሳቦችን አቅፎ ይዟል፡፡ የመጀመሪያው ሐሳብ ቁስል የመኖሩን እውነት መግለጹ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእኛን ቁስል ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ቁስል ማየት እንዳለብን ማስረገጡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ታሪክ ተፈጥረው በነበሩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ መዛነፎች ምክንያት የተለያዩ በደሎች በሕዝቦቻችን ላይ ደርሰዋል፡፡

እነዚህ በደሎችም በሕዝቦቻችን ውስጥ ጠባሳዎችን አሳርፈው፣ ቁስሎችን ትተው አልፈዋል፡፡ እነዚህ ቁስሎች በሚገባ ባለመታወቃቸው፣ ታውቀውም ባለመታከማቸው በየጊዜው እንደ አዲስ እያገረሹ ሀገራችንን ጤና እየነሷት ይገኛሉ፡፡
ግንቦት ሃያ እነዚህን ቁስሎች አውቀን የምናክምበት በዓል ሊሆን ይገባል፡፡ አንድን ቁስል ለማዳን መጀመሪያ ቁስሉንና የቁስሉን መነሻ በትክክል ማወቅ ይጠይቃልናም ብለዋል በመልዕክታቸዉ፡፡

ቁስሉን የግድ መለየት እና ማወቅ አለብን የምንልበት ምክንያት ቁስሉን በየጊዜው እየነካካን እንዲያገረሽ ለማድረግ አይደለም፡፡

ቁስልን በየጊዜው መነካካት እና ማከክ እንዲድን አያደርገውም፡፡ እንዲያውም ተባብሶ ጋንግሪን ይሆንና ሌላውን የአካል ክፍል በእጅጉ ይጎዳዋል፡፡ ቁስልን መነካካት ለሚነካካው ሰው አያመውም እንጂ፣ ለሚነካካበት ሰው ግን ከሕመም ውጭ የሚያተርፈው ነገር የለም፡፡

በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ቁስልን እያሳዩ ገንዘብ ለማግኘት መለመኛ ማድረግ ይፈልጉ ይሆናል፤ አንዳንድ ቁስልም ለጊዜው ሲያኩት ደስ ይላል፡፡ ያም ቢሆን ግን ለሕመሙ ፈውስ ለቁስሉም መዳን የሚያበረክተው አስተዋጽዖ አይኖርም፡፡ ቁስሉን በሚገባ ማወቅ ያለብን ለሁለት ነገር ነው፡፡

መጀመሪያ ራሳችንን በቆሰለው ሰው ቦታ ላይ አድርገን የሰውዬው ቁስል እንዲሰማን ያስችለናል፡፡ የሰውዬው ቁስል ከተሰማን በሰውዬው ላይ አንፈርድም፣ አንቆጣም፣ በቁስሉ ምክንያት የሚሰሙትን ስሜቶችም በትክክል እንረዳቸዋለን፤ እንታመማቸዋለንም፡፡

ሁለተኛው ቁስሉን እናውቅ ዘንድ የሚያስገድደን ምክንያት ቁስሉን በሚገባ አክመን ለማዳን እንድንችል ነው፡፡ ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነውና፡፡ የማናውቀውን ቁስል ልናክመው አንችልም፡፡ ያልታወቀን ቁስል ማከም ሌላ ያልታወቀ በሽታ ማምጣት ነው፡፡

የቁስሉ ምንጭ ከታወቀ በኋላም “ማወቁንስ አዉቄአለሁ እጄ አጠረ እንጂ” በማለት እጃችን አጣጥፈን መቀመጥ ከንፈር መጠጣ እንጂ ሕክምና አይሆንም፡፡ ቁስሉ ይሽር ዘንድ ለመፍትሔውም በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።

አዎ! በሀገራችን ተፈጥረው የነበሩትን ቁስሎች በጋራ ዕውቅና ሰጥተን እንደ ሕዝብ በጋራ ለማዳን መነሣት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ‹እኔም አለኝ ቁስል፣ ያንተን የሚመስል› የሚለው አባባል የሚነግረን ሁለተኛው ጉዳይ እንደ ሕዝብ በደል ያልደረሰበትና ያልቆሰለ ወገን አለመኖሩን ነው፡፡ አቁሳይ ገዥዎች እንጂ አቁሳይ ሕዝብ የለም፡፡

የሚቆስል ሕዝብ እንጂ የሚቆስል ገዥም የለም፡፡ ሁላችንም ተበድለናል፤ ሁላችንም ቆስለናል፡፡ የእኛ ቁስል የነዚያን የሚመስል ነው፤ የእነርሱም ቁስል የእኛን የሚመስል ነው፡፡ ስለዚህም እርስ በርሳችን ዳግም መቋሰል አያስፈልገንም፡፡ ገዥዎቻችን በቂ ቁስል አሳርፈውብናል፡፡ አሁን ተጋግዘን መድኃኒቱን መፈለግ አለብን፡፡ መነሻችን ‹ያልቆሰለ የለም፤ ስለዚህም ሁሉም መድኃኒት ያስፈልገዋል› የሚል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

አንዱን ሕዝብ አቁሳይ፣ ሌላውን ሕዝብ ቆሳይ አድርገው የሚያሳዩ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ ነው፡፡

የሀገራችንን ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታ፣ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት ያላቸውን ርቀት፣ የድህነት ወለላቸውንና ለድርቅና ለተፈጥሮ አደጋ ያላቸውን ተጋላጭነት በማየት ብቻ ችግርና መከራ አንድ ያደረጋቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ለማወቅ ይቻላል፡፡

ድህነት፣ መከራ፣ ጦርነት፣ ረሐብና ቸነፈር በሁላችንም ላይ ጥለውት ያለፉት ጠባሳና ሰንበር አሁንም ይታያል፡፡ ይህ ጠባሳና ሰንበር ጀርባው ላይ ያላረፈበት ሕዝብ በዚህች ሀገር የለም፡፡

‹እኔም አለኝ ቁስል፣ ያንተን የሚመስል› የሚለው አባባላችን በውስጡ ፍቅር፣ መተሳሰብና መተዛዘንን ይዟል፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝቦች ሁሉ ጠባይ ነው፡፡ ‹አንተም አለህ ቁስል የኔን የሚመስል› አላለም፡፡ እኔ አንተን እመስላለሁ ነው ያለው፡፡ መጀመሪያ ለዚያኛው ወገን ሕመም ነው ዕውቅና የሰጠው፡፡

ወገኔ ታመመብኝ ብሎ ነው የተነሣው፡፡ ‹እኔን፣› እንደሚለው ባሕላችን ‹እኔም እንዳንተ ታምሜያለሁ፤ አብረን መድኃኒት እንፈልግ› ነው የሚለው፡፡ ሀብት ባያገናኘንም ሕመም አገናኝቶናል ነው የሚለው፡፡ እኛንም ከደስታ ይልቅ መከራ፣ ከጤና ይልቅ በሽታ አስተሣሥረውን መኖራቸው እሙን ብለዋል በመልዕክታቸዉ ፡፡

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች!! ታድያ ያለፉት ዘመናት ያቆሰሉን አይበቃንም እንዴ? ለምን አንድ ሆነን መድኃኒቱን አንፈልግም፡፡ እርስ በርሳችን ቁስላችንን እየነካካን እንዲያገረሽና ከማይድንበት ደረጃ እንዲደርስ ለምን እናደርገዋለን? ይህን በዓል ‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድ› የሚለውን ትተን ‹እኔም አለኝ ቁስል፣ ያንተን የሚመስል› የምንባባልበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *