ገንዳውኃ አካባቢ በመከላከያ አባላት ደረሰ የተባለውን ጉዳት የሚያጣራ ቡድን በአስቸኳይ እንደሚላክ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታውቀዋል
ገንዳውኃ አካባቢ በመከላከያ አባላት ደረሰ የተባለውን ጉዳት የሚያጣራ ቡድን በአስቸኳይ እንደሚላክ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ በምዕራብ ጎንደር ዞን የተከሰተውን ችግር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ማጣራቱ የሚካሄደው ከፌዴራልና ከሚመለከታቸው አካላት በተውጣጣ ቡድን ነው ብለዋል።
እንደ ርዕሰመስተዳድሩ አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት መኪኖቹን ከአንደኛው ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ በሞከረበት ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል ፡፡
ከአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ አንጻር የተቋራጩን ተሽከርካሪዎች አጅቦ ይጓዝ የነበረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነበር ያሉት አቶ ገዱ ያም ሆኖ የተፈጠረው ክስተት ግን መሆን ያልነበረበት ነው ብለዋል።
ችግሩ ቢያጋጥም እንኳ በትዕግስትና በውይይት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት መደረግ እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡
በተፈጠረው ግጭት በግጭቱ ውስጥ ምንም ሚና ያልነበራቸው ዜጎች አሳዛኝ በሆነ መልኩ ተጎድተዋል፣ ንጹሃን ዜጎችም ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የጉዳቱ ዝርዝር ተጣርቶ ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የወሰዱ አካላት በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
በምዕራብ ጎንደር ቅማንት አካባቢ የእርስ በእርስ መገዳደል እየቀጠለ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ ተግባር ዓላማ ቢስና መዳረሻ የሌለው ነው ብለዋል።
ይህ ተግባር የአማራና የቅማንት ሕዝብን ለአደጋ ያጋለጠ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ በአስቸኳይ መቆም አለበት ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በአካባቢው ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ሕጋዊና ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚንቀሳቀስም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው።