loading
የግብርና ሚኒስቴር  በሰው ሰራሽ ዘዴ ሴት ጥጃ ብቻ የሚያስወልድ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው፡፡

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 የግብርና ሚኒስቴር  በሰው ሰራሽ ዘዴ ሴት ጥጃ ብቻ የሚያስወልድ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በይርጋለም ከተማ በይፋ ያስጀመሩት የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ  ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ በተመረጡ 58 ወረዳዎች ከዓለም ባንክ በተገኘ 176 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በወተት ላም፣ በዶሮ፣ በዓሣና በስጋ ከብት ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


ዶክተር ፍቅሩ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች፣ የእንስሳት መኖ ዘር፣ የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችና የግብዓት አቅርቦት አስተማማኝ የገበያ ትስስር መፍጠር  ላይ ትልቅ እመርታ እያስመዘገበ ነው።የቴክኖሎጂ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ጠቅሰው ከውጭ ሀገር የመጣ 6 ሺህ
የዘረ መል ዶዝ በሚኒስቴሩ በኩል ለክልሎች መሰራጨቱን ተናግረዋል።


ይህ ቴክኖሎጂ ሴት ጥጆች ብቻ እንዲወለዱ የሚያደርግ በመሆኑ የሀገሪቱን የወተት ምርታማነት በማሳደግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። በቀጣይም በእንሰሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በመኖ ዘር ቅርቦት እጥረት፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል  እንደሚሰራ ተናግረዋል።


የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጀንባ ዝርያ የማሻሻሉ ስራ ለዓመታት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰው ከአምና ጀምሮ ስራው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘውን የዘረ መል ዶዝ  ለሰባት ወረዳዎች በማሰራጨት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑንም  አመልክተዋል። በዚህ ዓመት 90 ሺህ ላሞችን ለማዳቀል ታቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት 56 ሺህ ላሞችን ማዳቀል እንደተቻለ ተነግሯል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *