loading
የደንበጫው “የካናቢስ ፋብሪካ” ግንባታ እቅድ አነጋጋሪ ሆኗል

የደንበጫው ካናቢስ መድሃኒት ፋብሪካ እቅድ አነጋጋሪ ሆኗል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ወረዳ ሊገነባ ነው የተባለው የካናቢስ መድሃኒት ፋብሪካ ፍቃድ የሰጠው አካል የለም ተባለ።

የደምበጫ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽህፈትቤት በፌስቡክ ገጹ የካናቢስ መድሃኒት ፋብሪካ በወረዳው ሊገነባ መሆኑን በመግለጽ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያሰራጨው ደብዳቤ እና የሰራው ዘገባ በማህበራዊ ሚዲያ ዘንድ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል።

ጽህፈት ቤቱ አስቀድሞ ባሰራጨው መረጃ በወረዳው የሚገነባው የካናቢስ መድሃኒት ፋብሪካ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደርበትና ምርቱም የማይባክን ነው ካለ በኋላ ወደውጪ የሚላክ መሆኑን በመግለጽ ለወደራው ወጣቶች ገን ከፍተኛ የስራ ዕድል አንደሚፈጠር አትቶ ነበር።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎችም ከፋብሪካው ባለቤቶች የተሰጣቸውን ገለጻ በማድመጥ ለፋብሪካው ገንባታ የበኩላቸውን ድጋፍ አንደሚያደርጉ በመግለጽ “ይህ ለእኛ ዕድል ነው ልንጠቀምበት ይገባል” ማለታቸውንም ጽህፈት ቤቱ በመረጃው አካትቶታል።

በማህበራዊ ሚዲያ የዚህ ፋብሪካ ምንነት እና በህግ የተከለከለ አደንዛዠ እጽ ለመድሃኒት ማምረቻነት ሊውል ነው የመባሉ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ብዙዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙበት ቆይተዋል።

ይህንን ተከትሎ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በዚያው ፌስቡክ ገጹ ማስተባበያ አውጥቷል። በዚህም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለአማራ ማስሚዲያ ኤጀንሲ በላከው ደብዳቤ “ሀላፊነት በጎደለው መንገድ በሀገርና በዜጎች ጤንነት ላይ አደጋ የሚያደርስ ካናቢስ የተባለው እጽ ፋብሪካ ደምበጫ ላይ እንዲከፈት እንደ ክልልም ይሁን እንደ ከተማ ፈቃድ የሰጠ የለም” ማለቱን አመለክቷል።  ከክልሉ እውቅና ውጭ ሌላ ፈቃድ የሰጠ አካል ካለም አጥብቀን የምንቃወምና እንዲመልሱ የምናደርግ መሆኑን እናረጋግጣለን ማለቱም ተገልጿል።

የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ “ ለወረዳችን ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ለሚፈጥረው ፋብሪካ ግንባታው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ሁሉ ትብብርና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ለመጠቆም እንወዳለን” ባለ በማግስቱ የክልሉ ኢንደሰትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ፋብሪካው የማን አንደሆነና ማን እንደፈቀደለት አላውቅም ማለቱ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል።

በርካታ ሰዎች እንዲህ ያለ ክፍተት ጉዳት ከማስከተሉ በፊት በክልሉ አስተዳደር እና በወረዳው መካከል መናበብ ሊኖር ይገባል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል። ለዚህ ፋብሪካ ፈቃድ ተሰጥቶት ከሆነ ፈቃጁ አካል ማን አንደሆነና በምን አግባብ ፍቃድ አንደተሰጠው ሁሉም ዜጋ ሊያውቅ ይገባል የሚል አስተያየት የሰጡት ብዙዎች ናቸው።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *