loading
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት እንዲያወግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት እንዲያወግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ክልል በአስገዳጅ ሁኔታ ነዋሪዎችን ከታዳጊ እስከ አዛውንት ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ በማጋለጥ ላይ ይገኛሉ ብሏል ሚኒስቴሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በተግባራዊ እርምጃዎቿ እያሳየች መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣  ሰብዓዊ ዓላማ ያለው የተኩስ ማቆም መደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በአብነት አንስተዋል፡፡


ከዚህም ባሻገር ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችና ሌሎችም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ዙሪያ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።መንግስት አሁንም ለሰላም ያለውን አቋም የሚያሳዩ ግልፅ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለተለያዩ የዓለም ማህብረሰብ አካላት የማስረዳቱ ስራ ቀጥሏል ነው ያሉት። ሆኖም መንግስት ለሰላም በርካታ ርቀቶችን እየተጓዘ ቢሆንም አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።


ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን የህወሃትን የዳግም ጦርነት ዝግጅትና የታጣቂ ምልመላ በትክክል ተገንዝቦ  በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። በመሆኑም ለመንግስት የሰላም ጥረት በጎ ምላሽ አለመስጠትና ማጣጣል፣ ምንም እንዳልተሰራ የሚነገሩት ነገሮች ተገቢ ባለመሆናቸው ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ አፉን ሞልቶ እንዲነግራቸው ያስፈልጋል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *