የካፍ ኮንፌዴሬሽን የፍፃሜ ተፋላሚዎች ተለይተው ታውቀዋል
የ2018/19 የቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ፤ የፍፃሜ ተፈላሚ ቡድኖች ትናንት በተካሄዱ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡
በዚህም ትናንት በሁለቱ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ኢትዋል ዱ ሳህል እና ዛማሊክ መካከል በስታደ ኦሊምፒክ ደ ሱስ የተደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ፤ የግብፁ ቡድን ዛማሊክ በመጀመሪያው የአሌክሳንድሪያ ጨዋታ ወቅት በሜዳው 1 ለ 0 መርታቱን ተከትሎ በ1 ለ 0 ድምር ውጤት የቱኒዚያውን ቡድን በመጣል ለፍፃሜ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ሌላኛው ግጥሚያ የሞሮኮው ቤርካኔ በሜዳው ስታዴ ሙኒሲፓል ዴ ቤርካኔ የቱኒዚያውን ሲ.ኤስ ሴፋክሲያንን አስተናግዶ 3 ለ 0 በመርታት ለፍፃሜ ጨዋታው መብቃት ችሏል፡፡
በመጀመሪያው ጨዋታ ሴፋክሲያን 2 ለ 0 ያሸነፈ ቢሆንም የሞሮኮው ቡድን ውጤቱን ቀልብሶ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍፃሜ መድረሱን አረጋግጧል፡፡
ኮጆ ፎ ዶህ፣ ኦማር ኢናማሳይ እና ኢሱፉ ዳዮ ቤርካኔን ወደ ዋንጫው ጨዋታው ያሻገሩ የድል ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት የ2018/19 የቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ተጫዋቾች ሲለዩ፤ ኤስፔራንስ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ እንደሚገናኙ ታውቋል፡፡
የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ ወደ ኮንጎ ተጉዞ ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ያለግብ ቢለያይም በመጀመሪያው ጨዋታ ቱኒስ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 ረትቶ አልፏል፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው የሞሮኮው ዋይዳድ አትሌቲክ/ ዋይዳድ ካዛብላካ ደግሞ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በተመሳሳይ ያለግብ በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቅቋል፤ ዋይዳድ ሞሮኮ ላይ 2 ለ 1 በመርታቱ በዚሁ ድምር ውጤት ለፍፃሜው በቅቷል፡፡