loading
የኪነጥበብ ባለሞያዎች ለሰላም እሴት ግንባታ ቁልፍ ሃይል ናቸው ተባለ

አርትስ 18/03/2011

ኪነ ጥበብን ለሰላም በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴር ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር  ጋር በጋራ የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል ፡፡

በመድረኩ  የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያቤት ድኤታዎች እንዲሁም በርካታ የኪነጥበብ ባለሞያዎች መሳተፋቸውን ተመልክተናል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት እንደተናገሩት የኪነጥበብ ባለሞያዎች ፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር፣የሰላም እሴትን ለመገንባት ቁልፍ ሃይል ናቸው ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ እየተጓዘች ቢሆንም በተለያዩ  አካባቢዎች የሰላም እጦት ችግር እየሆነብን ነው ያሉት ሚኒስትሯ ፤ያጋጠመው ችግር ወቅታዊ እና የሚታለፍ ቢሆንም ሃገር እና ህዝብ ተጨንቀዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኪነጥበብ ስብራትን የመጠገን እና ወደ እያንዳንዱ ሰው የመድረስ ሃይል ስላለው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለማስተተካከል  ባለሞያዎች የዜግነት እና የሞራል ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው አለመግባባትን ለመፍታት፣ሀገራዊ ፍቅርን በትውልድ ውስጥ ለማስቀረት ፣ከምንጠቀምባቸው  መሳሪያዎች ዋነኛው ኪነጥበብ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ ከኪነጥበብ ባለሞያዎችም ኢትዮጵያን ሰላሟ የተረጋገጠ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረው ዘርፉ እንዳይስፋፋ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችንም የሚመለከታቸው አካላት እንዲያስተካክሏቸው ሀሳብ አንስተዋል፡፡

ባለሞያዎቹ በቀጣይ ከሰላም ሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር በጋራ ስለሚያከናውኗቸው  ስራዎችም ተወያይተዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *