የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አመታት ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ የ54 ቢሊዮን ብር እዳ የመክፈል ፈተና እንደገጠመው ተገለጸ፡፡
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አመታት ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ የ54 ቢሊዮን ብር እዳ የመክፈል ፈተና እንደገጠመው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በስምንት ቢሊዮን ብር በጀት የአምስት ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
ይህ የተጀመረው የቤቶች ፕሮጀክት በተገጣጣሚ ቴክኖሎጂ የሚሰራና በአጭር ጊዜ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ነው ተብሏል።
ከንቲባዋ በፕሮግራሙ ማስጀመርያ ላይ ባደረጉት ንግግር በከተማችን የነዋሪዎችን መሠረታዊ የቤት ጥያቄ ለመፍታት ብዙ ጥረቶችና ዝግጅቶችን አድርገናል ብለዋል፡፡
በረጅም ዓመታት የተገነቡ ቤቶች በተለይም ሰፊ የሃብት ብክነትና በማስተላለፍም በኩል በርካታ ችግሮች እንደነበረባቸው ገልፀዋል፡፡ ይህም በተለይ አስተዳደሩ ባለፉት አመታት በቤቶቹ ምክንያት የተከማቸ የ54 ቢሊዮን ብር እዳ መክፈል ፈተና ገጥሞት እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡
ስለሆነም ካለፈው ትምህርት ተወሶዶ በአጭር ጊዜ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን በመገንባት የነዋሪዎችን የቤት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ቤቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ በከተማ ደረጃ የተያዘውን ቤቶችን ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ በከፊል የሚያሳካ ይሆናል ነው የተባለው፡፡
ኘሮግጀክቱ የተሻለ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ከማስፋፋት በተጨማሪ በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ከከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ሃብታችንን ያለብክነት ለመጠቀም ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ሁላችንም የወሰድነውን የህዝብ ሃላፊነት በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ከንቲባዋ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡