loading
የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ መፅደቅ ኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥገኛ የሚያደርግ በመሆኑ እንዳይፀድቅ ሁሉም ሊሰራ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጠየቁ።

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ መፅደቅ ኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥገኛ የሚያደርግ በመሆኑ እንዳይፀድቅ ሁሉም ሊሰራ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጠየቁ። አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ስታተርፊልድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል። በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገች መሆኑን ማስረዳታቸውን ጠቅሰው፥ ኤች አር 6600 የአሜሪካን እና የኢትዮጵያን ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን ነግረዋቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ረቂቁ እንዳይፀድቅ ጥሪ ማቅረባቸውንም ነው የገለጹት። የአሜሪካ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ባስ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንም በዚህ ወቅት አንስተዋል። የአሜሪካ መንግስት ጫና ለመፍጠር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መፈተሽ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል። ኦክስፋም የተሰኘው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ
እንደሚቀጥል መግለጹንም ጠቅሰዋል። ከደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳዎች ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ፥ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚያስችል ውይይት መካሄዱን አስረድተዋል።

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ከኢድ አል አድሃ እስከ ኢድ አል ፈጥር የተሰኘው ታላቁ ጉዞ ወደ ሃገር ቤት መርሃ ግብር ከሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታው ባሻገር ኢትዮጵያውያን ተቀራርበው በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲመካከሩ የሚያስችል ታላቅ አላማን ያነገበ መሆኑን አመላክተዋል። ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘም በሳዑዲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እያፋጠነ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *