የአፍሪካ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዛሬ ምሽት ይደረጋል
የ2019 የቶታል ካፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ (ሱፐር ካፕ) ጨዋታ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ውጪ በኳታሯ አል ራያን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ታሀኒ ቢን ጃሲም ስታዲየም ዛሬ ምሽት 1፡00 ይከናወናል፡፡
ጨዋታው በ2018ቱ የቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ እና በ2018ቱ ቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ባለድል የሞሮኮው ራጃ ክለብ አትሌቲክ ወይንም ራጃ ካዛብላንካ መካከል ይደረጋል፡፡
በ2022 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ውድድር በምታሰናዳው ኳታር የሚካሄደውን ይሄንን የአሸናፊዎች አሸናፊ ግጥሚያ፤ በአህጉሩ ትልልቅ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ሃላፊነት ከሚሰጣቸው ጉምቱ ዳኞች መካከል አንዱ በሆኑት፤ ኢትዮጵያዊው ዓለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ ወየሳ በመሀል አርቢትርነት እንዲመሩት ተመድበዋል፡፡
ኤስፔራንስ በቻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ የግብፁን አል አህሊን 4 ለ 3 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ዋንጫውን ሲያነሳ፤ ራጃ ካዛብላንካ ደግሞ የኮንጎውን ኤ. ኤስ ቪታ 4 ለ 3 ረትቶ አሸናፊ ሁኗል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ማንሳት ችለዋል፡፡
አል አህሊ ዋንጫውን ስድስት ጊዜ ያህል በማሸነፍ ቀዳሚው ቡድን ሲሆን ቲፒ ማዜምቤ እና ዛማሊክ በሶስት ድሎች ይከተላሉ፡፡