የአውሮ ቻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይከናወናሉ
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ዛሬ ይጀመራሉ፡፡
ዛሬ ምሽት 4፡ 00 ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ሁለት ጨዋታዎች ሲከናወኑ፤ ሶስት የእንግሊዝ ክለቦች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
የፖርቱጋሉ ክለብ ፖርቶ ወደ እንግሊዝ ምድር ተጉዞ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ከሊቨርፑል ጋር ይፋጠጣል፡፡
በጥሎ ማለፉ ውድድር ቀያዮቹ ባየርን ሙኒክን እንዲሁም ፖርቶ የጣሊያኑን ሮማ በመጣል ነው ለዚህ ዙር መብቃት የቻሉት፡፡
በምሽቱ ጨዋታ ሊቨርፑል ቅድሚያ የማሸነፍ ዕድል አግኝቷል፡፡
በሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ቶተንሃም ሆትስፐር በአዲሱ ስታዲየም የመጀመሪያ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን ማንችስተር ሲቲን በማስተናገድ ይጀምራል፡፡
በሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች መካከል የሚደረገው ይህ ግጥሚያ ውጤት ላይ፤ አስቀድሞ ቢያንስ አንድ የእንግሊዝ ክለብ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ውድድር እንደሚበቃ እርግጠኛ መሆን የተቻለበት ነው፡፡
በዚህ ተጠባቂ ግጥሚያ ሲቲ ለአራት ዋንጫዎች ስኬት እያደረገ ያለውን ጉዞ እውን ለማድረግ አሸናፊ መሆን፤ አሊያ ለመልሱ ጨዋታ ጥሩ ውጤት ይዘው መመለስ ይጠበቅበታል፡፡
ለቶተንሃም ደግሞ ለአዲሱ ስታዲየም ገቢ እንደ ቻምፒዮንስ ሊግ ያሉ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ውጤት ግድ የሚለው በመሆኑ ለሀገሩ ክለብ በቀላሉ ይንበረከካል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡
ሁለቱም ክለቦች የጀርመን ቡድኖችን ጥለው ነው ወደ ሩብ ፍፃሜው የተቀላቀሉት፡፡
ማንችስተር ሲቲ ሻልከን እንዲሁም ቶተንሃም ቦሩሲያ ዶርትሙንድን በሰፊ የግብ ልዩነት ጭምር በመርታት አሁን ያሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡