loading
የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ወኪልነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለመጡበት ተቋምና ማንነት አይደለም ተባለ

የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ወኪልነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለመጡበት ተቋምና ማንነት እንዳልሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ኮሚሽኑ በጥናት ላይ የተመሰረተና ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር እንዲያከናውን ጥሪ ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስራው ላይ መንግስታዊ ጣልቃገብነት እንደማይኖርበትም አረጋግጠዋል።

ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ጋር የተካሄደውን የመጀመሪያ የትውውቅና የስራ ምክክር መድረክ የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት ኮሚሽኑ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት በመሆን ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ የወሰን ማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አልሞ የተቋቋመ ነው።

ከወጣት እስከ አዛውንት ያካተተው የኮሚሽኑ አባላት ስብጥርም ኃይማኖትን፣ ፃታንና የትውልድ አካባቢን እንደዚሁም ልምድና ዕውቀትን ባገናዘበ መልኩ የተዋቀረ ነው ብለዋል። ያም ሆኖ አባላቱ ወኪልነታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ለመጡበት ማንነትና ተቋም አይደለም ብለዋል። ስለሆነም ከኮሚሽኑ ገለልተኛ አሳታፊና በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት።

 

ኮሚሽኑ የሚፈለገውን ተልዕኮ ለማሳካት የራሱን አደረጃጀት መፍጠር፣ ንዑሳን ኮሚቴ ማዋቀርና የስራ ክፍፍል ማድረግ እንዲሁም መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚችልም ተናግረዋል።በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአሰራር ደንብ ይወጣለታል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆንም የሰላም ሚኒስትር አስፈላጊ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግለትም በውይይት ላይ ተገልጿል። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ከአባላት መካከል ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በቅርቡ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ ፤ ለኮሚሽኑም ጽህፈት ቤት ይቋቋምለታል ተብሏል ።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *