loading
የአማራ ክልል በህወሓት ላይ የተጀመረው “ሕግን የማስከበር” ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ::

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 7፣ 2013  የአማራ ክልል በህወሓት ላይ የተጀመረው “ሕግን የማስከበር” ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ:: በትግራይ ክልል በህወሓት ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርግ የአማራ ክልል ጠየቀ፡፡ ክልሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ “ትህነግ አገር ከማፍረስ እኩይ ተልዕኮው ሊታቀብ የሚችለው የአገራችንን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በጽናትና በአላማ ቁርጠኝነት በጋራ መጠበቅ ስንችል ነው”
ብሏል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ወቅት በጋራ እንዲቆም ክልሉ ጠይቋል። ክልሉ፤ በየትኛውም ዘመን ሰልጥነው በማንኛውም የመንግስት ጸጥታ መዋቅር ውስጥ በመግባት ሲያገለግሉ የቆዩና አሁን ያንን ሙያቸውን የቀየሩ ዜጎች የክልሉን ጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም በየትኛውም የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩና አሁን በዚህ ስራቸው ላይ የሌሉ ዜጎች በየአካባያቸው ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት በአካል በመገኘት በፈቃደኝት ሊመዘገቡ እንደሚችልም ገልጿል። አሁን ላይ ያለው አደጋ ያለበቂ ዝግጅትና ደረጃውን ከጠበቀ ስልጠና ውጭ መሆን እንደሌለበት ያነሳው
መግለጫው ወጣቶች ከማንኛውም ግብታዊ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ፤ በየደረጃው ለሚኖረው ምልመላና ስልጠና በመሳተፍ በቂ ዝግጅት እንዲየደርጉና የመንግስትን ጥሪ እንድጠባበቁ ክልሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አሁን ላይ የተጀመረው ትግል የሁሉም አንድነት፣ ህብረትና ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠይቅም ያነሳው መግለጫው፤ በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ ማህበራዊ አንቂዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች በሕብረትና በጋራ እንድቆሙ ጠይቋል። የክልሉ ሕዝብ፤ በከተማና በገጠር የሚገኙ ነዋሪዎች፤ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ምሁራንና የክልሉ ተወላጆች፣ በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች የተጀመረው “የህልውና
ትግል” እንዲያግዙም ክልሉ ጠይቋል፡፡

ክልሉ እየተደረገ ያለውን ትግል እንደሚያሸንፍ ገልጾ፤ ሁልጊዜም ቢሆን የአማራ ክልል ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ውጭ እንደማይሳካ እንደሚገነዘብ አስታውቋል። ክልሉ እንዳለው፤ የሚደረገው ትግል ለኢትዮጵያ፤ ሉአላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝብ የህልውና ትግል
እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ እንዳልሆነ ገልጿል። የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ፤ከእብሪት ይልቅ ድርድርን እንደሚያስቀድም መግለጫው ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ “ህወሓት ሕዝብና ሀገርን ለማዋረድ የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት እናሳስባለን” ሲልም ገልጿል ክልሉ፡፡ ህወሓት፤ ትግራይ ክልል እና አማራ ክልል በሚዋሰኑባቸው ሁሉም አቅጣጫዎች “መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት” እየፈጸመ እንደሚገኝ ያነሳው መግለጫው ህወሃት “አረመኔና ጨካኝ ቡድን“ መሆኑ ሊታወቅ
እንደሚገባ ገልጿል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *