loading
የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም አሉ

የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም አሉ

ህገመንግስቱ እንዲከበርለት የሚጠይቅ ህዝብ ራሱ ህግን በማክበር ቅድሚያ መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል

ም/ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረጽዮን ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር አካባቢ ለመልቀቅ ከባድ መሳሪያዎችን ጭኖ የተንቀሳቀሰው የመከላከያ ሰራዊት ኮንቮይ እንቅስቃሴ በሽሬ አካባቢ በገጠመው የነዋሪዎች ተቃውሞ መስተጓጎሉን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሰራዊቱ እንቅስቃሴ ህጋዊ ነው ብለዋል።

ስለሆነም ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊቱ እንቅስቃሴ ሳይረበሽ ወደልማት ስራው እንዲያተኩር መክረዋል።

ህዝቡ የሚያነሳው የህገ-መንግስት ይከበርልን ጥያቄ እራሱ ህግን ከማክበር መጀመር የሚገባው መሆኑንም ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ እንዳሉት የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ህጋዊና ኃላፊነቱንም ለመወጣት የሚያስችለው ተግባር ነው።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ ይሄንን ተገንዝቦ ያለምንም መረበሽ የልማት ስራውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን አለበት።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ባደረጉት የጋራ ስምምነት የሁመራ ኦምሃጀር መንገድ መከፈት ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚ እንደሆነም ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስከበርን ጉዳይ በተመለከተም ህዝቡ በፈጠረው አደረጃጀት አንድነቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል። መንገዱ የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈው ቀጣይ ህጋዊ መስመር ለማስያዝም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።መረጃው የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *