የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ጉዳይ የብሄራዊ ኩራት ጉዳይ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ጉዳይ የብሄራዊ ኩራት ጉዳይ መሆኑን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሪፖረት አቅርበዋል።
በሪፓርቱ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከህብረተሰቡ በቦንድ ሽያጭ እና ከዳያስፓራው ማህብረሰብ እስከ 2011 ዓመተ ምህረት 12 ነጥብ 31 ቢሊየን ብር እንደተሰበሰበ ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 46 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በስጦታና በተለያዩ መንገዶች እንደተሰበሰበ ተነግሯል።
በዚሁ ወቅት ህብረተሰቡ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በዚህ ሪፓርት ለግንባታው መጓተት የልምድ ማነስ፣ ለመማር ዝግጁ አለመሆን እና ለሚኒሱ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት በምክንያትነት ተነስተዋል።
እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተመርተው ለግንባታ የዋሉ ቁሳቁሶች የጥራት ጉድለት እና የኃይል ማመንጫ ተርባይነሮች በየቦታው ተበታትነው መቀመጥ ለአስተዳደር አስቸጋሪ እንዳደረገው ተጠቁሟል።
የህዳሴ ግድብ ታህሳስ 2013 ዓመተ ምህረት የመጀመሪያውን ሀይል እንዲያመነጭ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን፥ የሀይል ማመንጫው በ2015 ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
ባለፉት ሰባት አመታት አርሶ አደሩ በአከባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ስራ መስራቱ ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው፡፡
ሚኒስትሩ ለሳሊኒ እና ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለኮንትራት የተፈፀመን ክፍያ ለምክር ቤት አባላት አቀርበዋል።
በዚህም ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖራሽን ጋር 25 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውል መፈረሙንና የ16 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ክፍያ መፈፀሙን አንስተዋል።
የክፍያ አፈፃፀሙም 65 በመቶ ሲሆን የስራ አፈፃፀሙ ደግሞ 23 በመቶ መሆኑ ነው የተመለከተው።
ሳሊኒ ኮንስትራክሽንን በተመለከተም 81 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ክፍያ እንደተፈፀመና አፈፃፀሙም 82 በመቶ እንደሆነ በሪፓርቱ ተመልክቷል።
በአጠቃላይ ግድቡ ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከታቀደው ተጨማሪ ወጪ ሀገሪቱን እንድታወጣ ማስገደዱ እንደማይቀር ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ዘገባው የፋና ነው