loading
የቱርክ የፊልም ኢንዱስትሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እያጠናከረ ነው-ጠ/ሚ ዐቢይ::

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13፣2013 የለውጥ ሂደቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያና ቱርክ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በጋራ እየሰሩ ነው:: ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ  ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። በቱርክ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በመግለጫቸው ሁለቱ አገሮች ያላቸው ግንኙነት ወንድማማችነት ነው ብለዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ልዑክ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ  መምከራቸውን ገልጸዋል።ከመከሩበት ጉዳይ መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል። የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ኢንቨስትመንት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸው፤  ይህንን ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ መምከራቸውን ተናግረዋል።

በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት የሚያደርጉ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለኩባንያዎቹ ድጋፍ እያደረገች ስለመሆኗም ገልጸዋል። በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን፤ “የኢትዮጵያ ሰላም መሆን እኛን ጨምሮ ለሁሉም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ግጭቶች እንደሚፈቱ  ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መፈታት እንደሚገባው የተናገሩትፕሬዚዳንቱ፤ ቱርክ ማደራደርን ጨምሮ ሰላም ለማምጣት የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በበኩላቸው ቱርክ በምሳሌነት ሊወሳ በሚችል የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ማለፏን ጠቅሰው፤ በሁሉም ዘርፍ ወጥነት ያለው እድገት ማስመዝገቧን እንደቀጠለች ተናግረዋል። የቱርክ የፊልም ኢንዱስትሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *