loading
የስፔን ላ ሊጋ የ31ኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ይጠበቃሉ

በሊጉ ቅዳሜ አራት ግጥሚያዎች ሲከናወኑ፤ የሳምንቱ ተጠባቂ ፍልሚያ በላ ሊጋው የደረጃ ሰንጠራዥ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ መካከል ይከናወናል፡፡

ጨዋታው በካምፕ ኑ ምሽት 3፡45 ሲል ይጀመራል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የስምንት ነጥብ ልዩነት ያለ ሲሆን የካታላኑ ቡድን አሸንፎ ልዩነቱን ወደ 11 ለማስፋት፤ አትሌቲ ደግሞ ወደ አምስት ዝቅ ለማድረግ በምሽቱ ብርቱ ፉክክር ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በባለሜዳው በኩል ጀራርድ ፒኬ፣ ኢቫን ራኪቲች እና ሊዮኔል ሜሲ ከቪያሪያል ጋር በነበረው የሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታ ቅድሚያ የመሰለፍ ዕድል ያልተሰጣቸው ሲሆን በነገው ጨዋታ በቋሚ አሰላለፍ ይመለሳሉ፡፡ ፈረንሳያዊው ኦስማን ዴምቤሌ በጉዳት ምክንያት አሁንም ከጨዋታው ውጭ ነው፡፡

በነጭ እና ቀይ ለባሾቹ ወገን አጥቂዎቹ ዲዬጎ ኮስታ እና ቶማስ ሊማር ወደ ካታሎኒያ በሚደረገው ጉዞ ከቡድኑ ጋር የመጓዛቸው ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል፡፡

ነገ ምሽት 12፡15 ላይ ሪያል ማድሪድ ሳንቲያጎ ቤርናቤው ላይ ኤይባርን ያስተናግዳል፡፡

ራዮ ቫዬካኖ ከ ቫሌንሲያ እንዲሁም ጂሮና ከ ኢስፓኞል የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

ቀሪ የሳምንቱ ጨዋታዎች በበነጋታው ዕለተ ሰንበት ሲደረጉ ፤ አላቬስ ከ ሌጋኜስ፣ ሄታፌ ከ አትሌቲክ ቢልባዎ፣ ሪያል ቫያዶሊድ ከ ሲቪያ፣ ሴልታ ቪጎ ከ ሪያል ሶሴዳድ፣ ሌቫንቴ ከ ሁሴካ እና ሪያል ቤቲስ ከ ቪያሪያል ይገናኛሉ፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *