የሱዳን ተቃዋሚዎች ሪያድ እና አቡዳቢ ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ አስጠነቀቁ፡፡
የሱዳን ተቃዋሚዎች ሪያድ እና አቡዳቢ ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ አስጠነቀቁ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ሳውዲ አረቢያ ለአዲሱ የካርቱም መንግስት የ3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ማሰባቸውን ተከትሎ በዘመነ አልበሽር ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሱዳናዊያን ቅር ተሰኝተዋል፡፡
ሳውዲ ሱዳንን እደግፋለሁ የሚል መግለጫ መስጠቷ በተሰማ ቅፅበት በሱዳን መከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት የተኮለኮሉት ሰልፈኞች በሪያድ ላይ እርዳታሽን አንሻም በሚል ጩኸት ቁጣቸውን ሲገልፁ ተሰምተዋል፡፡
ምክንያትቸው ደግሞ ድጋፉ ይሄን ወቅት ጠብቆ የሚሰጠው ከጀርባው አንዳች ተንኮል ቢኖረው ነው የሚል መነሻ ያለው ነው፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ተቃዋሚዎቹ እነዚህ ሀገራት ለሱዳናዊያን አስበው ከሆነ ምነው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በወታደሮቻቸው ህዝባቸውን ሲያስጨርሱ ዝምታን መረጡ በማለት ሀገራቱን ይሞግታሉ፡፡
ሁለቱ የገልፍ ሀገራት በጋራ በሰጡት መግለጫ ከድጋፉ ገንዘብ 500 ሚሊዮን ዶላሩ በሱዳን ማእከላዊ ባንክ ተቀማጭ ተደርጎ ሀገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል፡፡
ቀሪው ገንዘብ ደግሞ በምግብ እና በመድሀኒት መልክ ወደ ካርቱም ይላካል ሲሉም አክለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሪያድ እና አቡዳቢ ስልጣን ለሲቪል አላስረክብም ብሎ የሚያንገራግረውን ወታደራዊ ካውንስል ለመደገፍ ማሰባቸውን ተቃዋሚዎቹ ፈፅሞ አይስማሙም ፡፡
መንገሻ ዓለሙ