loading
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ከማሊ ወታደራዊ አዛዦች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ተባለ::

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2013 የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ከማሊ ወታደራዊ አዛዦች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ተባለ:: የምእራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኩዋስ በማሊ መፈንቅለ መንግስት አካሂደው ሀገሪቱን እየመሩ ያሉት ጄኔራሎች ስልጣናቸውን በአስቸኳይ ለሲቪል እንዲያስረክቡ ያቀረበው ጥያቄ ቀና ምለሽ
አላገኘም፡፡ ኢኩዋስ ለወታደራዊ ጁንታው የሰጠው ቀነ ገደብ ያለፈ ሲሆን በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ ምርጫ ተደርጎ ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ ቢያሳስብም ጄኔራሎቹ ግን ይህን የጊዜ ገደብ ለተጨማሪ ስድስት ወራት አራዝመውታል፡፡

የጋናው ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ ድርድሩን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ከወታደራዊ አዛዦቹ ጋር መግባባት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ቢሆንም ግን የቀጠናው ሀገራት መሪዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ዳግም ድርድር ለማድረግ በቀጣዩ ሳምንት ቀጠሮ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ ኢኩዋስ በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን በአስቸኳይ የሲቪል መንግስት ካልተቋቋመ ሀገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ ልታመራ እንደምትችል ስጋቱን ገልጿል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው ማእቀቡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙ ድንበሮችን መዝጋትና የገንዘብ ዝውውርን ማገድን ያካትታል ተብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *