የምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሄደ
የምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ተካሄደ
አርትስ 11/04/2011
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ የዲሞክራሲ ተቋማት ጥናት ቡድን የተሰናዳ ሲሆን ከተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራን እና ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ዋና አላማ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በማድረግ ግብአት መሰብሰብና ቅቡል የሆነ አዋጅ እንዲሆን ለማስቻል ነው ተብሏል።
ለምክክር የቀረበው ረቂቅ አዋጅም 36 የሚሆኑ አንቀጾች የተካተቱበት ሲሆን፤ የቦርድ አባላት ሚና ላይ ቀድሞ ቦርዱን በቋሚነት የሚያገለግለው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ብቻ በሚለው አንቀፅ ላይ ሁሉም አባላት በቋሚነት በቦርዱ ውስጥ እንዲሰሩ የሚል ሀሳብ መካተቱ ተገልጿል።
እንደ ኤፍ.ቢ.ሲ ዘገባ የቦርዱ አባላት በቦርዱ ውስጥ የሚሰሩት የሙሉ ስራ ድርሻም በፅህፈት ቤቱ ቴክኒካል ስራዎች ላይ የተወሰነ ይሆናል።
ከዚህ በፊት የቦርዱ አባላት አሰያየም በጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቦ በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቅ እንደነበር ይታወቃል። በተሻሻለው ረቂቅ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጠኝ አባላትን የያዘ ገለልተኛ ኮሚቴ ያዋቅራል።
ኮሚቴውም ለቦርድ አባላት የሚያስፈልገውን የቁጥር መጠን በእጥፍ ጨምሮ በመመልመል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያቀርብ ይደረጋል ተብሏል።