loading
የሊቢያ የሰላም ጥሪ

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 29፣ 2012 ግብፅ የሊቢያ የሰላም ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቀረበች:: የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ካይሮ የትኛውንም የተኩስ አቁም ስምምነትና የሰላም ድርድር ሂደት ለመደገፍ ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡ ሽኩሪ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ ከፍተኛ ልዑክ ጆሴፍ ቦሬል ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው ይህን ያሉት፡፡

በእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው ሊቢያ ወደቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ ግብፅ ከአወሮፓ አጋሮቿ ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ግበፅ ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አልሳራጅ መንግስት ይልቅ በምስራቃዊ ሊቢያ ነፍጥ አንግበው ትሪፖሊን ለመቆጣጠር የሚተጉትን ጄኔራል ከሊፋ ሀፍታርን እንደምትደግፍ ነው የሚነገረው፡፡

በተለይ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ቱርክ ለትሪሊን መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ መጀመሯን ተከትሎ የድጋፍ ጥሪ ቀርቦልኛል በሚል ሰበብ የሀፍታርን ጦር እያገዘች ነው ተብሏል፡፡ ሲ ጂ ቲ ኤን እንደዘገበው በአሁኑ ጊዜ አንካራ እና ካይሮ በሊቢያ ጉዳይ ከፍተኛ እሰጥ አገባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሊቢያ ከፕሬዚዳንት ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን መወገድ ወዲህ በተለያዩ ፖለቲካዊ እና የጎሳ ክፍፍል ውስጥ ገብታ በእርስ በርስ ጦርነት ሰላሟ ከራቃት ውሎ አድሯል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *