loading
ኬንያ እና ሶማሊያ አሁንም በመልካም ጉርብትናቸው የሚቀጡሉበት መንገድ አልተዘጋም ተባለ::

አዲስ አበባ፣ጥር 03፣ 2013 ኬንያ እና ሶማሊያ አሁንም በመልካም ጉርብትናቸው የሚቀጡሉበት መንገድ አልተዘጋም ተባለ:: ሶማሊያ ባለፈው ዲሴምበር ወር በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገባችብኝ በሚል መነሻ ከኬንያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን በይፋ አቋርጣለች፡፡ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸው ወደ ነበረበት እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ የአፍሪካ ህብረትም ውዝግቡ በሰላም እንዲፈታ አሳስቦ ነበር፡፡

ሶማሊያ ውስጥ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ኬንያዊያን ሰራተኞች እንዳሉና በኬንያም በተመሳሳይ በርካታ ሶማሊያዊያን መኖራቸው ችግራቸውን በመቀራረብ እንዲፈቱ ግድ ይላቸዋል ነው የተባለው፡፡ ከዚህም በሻገር ሁለቱ ሀገራት ሰፊ ድንበር ስለሚጋሩ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮችም ከፍተኛ ትስስር አላቸው፡፡ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ሶማሊያ ሲልክ ኬንያ በርካታ ወታደሮቿን መላኳ የነበራቸውን የትብብር መንፈስ የሚያሳይ ነበር የሚሉት ፖለቲከኞች; አሁንም ከመስማማት ውጭ አዋጭ መንገድ የለም ሲሉ ይመክራሉ፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው ጎረቤታሞቹ በንግድ፣ በፀጥታ እና ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሳቢያ ውዝግብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ አሁን ላይ የሁለቱም ሀገራት መሪዎች ችግሩን በሰከነ መንፈስ ለመፍታት የጋራ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፤ ሀገራቱ ከነበራቸው ታሪካዊ ግንኙነት በመነሳት ሁኔታው ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *