እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው የንግድ ተቋማት…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 ግብይት ሳይኖር የደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የነበሩ 2 ድርጅቶችና 3 ግለሰቦች ከባድ የቅጣት ዉሳኔ
እደተላለፈባቸው ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ቅጣቱ የተወሰነባቸው አባቢን ኮንስትራክሽን እና ማሽነሪ ኪራይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና
ዲን ጀነራል ትሬዲንግ የተባሉ ድርጅቶች መሆናቸውን ሚስቴሩ ገልጿል፡፡ ከንግድ ተቋማቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 3 ግለሰቦችም የገንዘብና የእስር ቅጣት
ተወስኖባቸዋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
አቶ ቢኒያም አበበ፣ ደጀኔ ጆቫኒ እና አባይ መኮንን የተባሉት 3 ግለሰቦች ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም በኮንስትራክሽን ዕቃዎች ሽያጭና ማሽነሪ ኪራይ የንግድ ዘርፍ ተመዝግበው ሲሰሩ እንደነበር ተገልጿል፡፡ አባቢን ኮንስትራክሽን መጀመሪያ ምንም አይነት ግብይት ሳይኖር ወደ 129 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ፣ ቀጥሎ ደግሞ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ መፈጸሙ ተረጋግጧል ነው የተባለው፡፡
ዲን ጀነራል ትሬዲንግም በተመሳሳይ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት ሳይኖር የደረሰኝ ሽያጭ መፈፀሙ በኦዲት ተረጋግጦበታል፡፡
እንዲሁም ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ የግብር ስወራ ወንጀል ሲፈፅሙ በተጨማሪም 91 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግብር እንዳለባቸው አሳውቀው ባለመክፈላቸው ተከሰው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ሁለቱ ድርጅቶች እያንዳንዳቸው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ ቢኒያም አበበ እና ደጀኔ ጆቫኒ እያንዳንዳቸው 18 ዓመት ፅኑ እስራትና 1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡ እንዲሁም አባይ መኮንን የተባለው ተከሳሽ በ9 ዓመት ፅኑ እስራትና በ750 ሺህ ብር መቀጣቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡