ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በነበራት ቆይታ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን መስራቷ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በነበራት ቆይታ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን መስራቷ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሁለት ዓመት ቆይታዋ ወቅት ብሄራዊ ጥቅሟን ከማረጋገጥ ባለፈ የአፍሪካ አቋም በተለያዩ መድረኮች እንዲፀባረቁ ማድረጓን በተመድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ።
አምባሳደር ታዬ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት ቆይታዋ ወቅት ባስቀመጠቻቸው የትኩረት መስኮች መሰረት ብሄራዊ ጥቅም ያማከለ አቋም በማራመድ፣ በምክር ቤቱ አጋሮችን በማፍራት እና በአገራችን ለተጀመረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም ሁለንተናዊ የፖለቲካ ለውጥ ዓለማቀፋዊ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማስገኘት የሚያስችል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። በቀጣይ የተመድ አባልነታችን ወቅት ለምናካሂደው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሰፊ ትምህርት መቅሰም መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአገራት መካከል ያለ ግንኙነት መመራት የሚገባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እና ጸጥታ በታወቁ በተመድ ህግጋት እንዲመሩ በማድረግ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ አቋም በመውሰድ፣ ለሀገራዊ ጥቅሞች ቅድሚያ በመስጠት በአገራት መካከል ላለው ግንኙነት ገለልተኛ አቋም በመንጸባረቅ፣ የተመድ ቻርተር መርሆችን በማክበር እና በማስከበር፣ በአፍሪካ ህብረት የተወሰኑ ውሳኔዎችን ማክበር እና ማስከበር፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ግጭቶችን መፍታት የሚቻለው ከተናጠል ይልቅ በባለብዙ አማራጭ የተሻለ ውጤታማ መሆኑን አምባሳደሩ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረሰው ስምምነት ተከትሎ ኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ መደረግ፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን አብዮ ግዛት የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ዘላቀ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ እንዲራዘም መደረጉ፣ ዳርፉር የሚገኘው የሰላም ሁኔታ የበለጠ እንዲጠናከር መሰራቱን፣ የቡሩንዲ አሩሻ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሶማሊያ ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት ተከታተይ ውይይት እንዲደረግ፣ መካከለኛው ምስራቅ በየመን፣ በሶሪያ፣ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ዙሪያ ዘላቂ የመፍትሄ ሀሳቦችን ኢትዮጵያ ማቀረቧን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።