ኢትዮጵያዊነት የተዘጉ በሮችን ማስከፈት የሚችል እውነት ነው- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2013 የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ኢትዮጵያዊነት የተዘጉ በሮችን ማስከፈት የሚችል እውነት ነው ሲሉ ገለጹ። ምክትል ከንቲባዋ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት እየተከበረ ያለውን የኢትዮጵያዊነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ በሚገኘው መርሐ-ግብር ላይ ነው። ዛሬ እየተከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያዊነት ቀን ከመስቀል አደባባይ ሥነ-ሥርዓት መልስ በሸራተን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ በዚህ ሥነ- ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያዊነት ሀቅ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት እውነትን መፈለግ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ የሰውን አለመፈለግ ብሎም የራስን አሳልፎ አለመስጠትም ነው ብለዋል፡፡ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያዊነት እንደ ከበረ እንቁ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት የተቀመጠ ከዘመናት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በእሳት ተፈትኖ የነጠረ፣ በተግባር ተፈትኖ የከበረ ስም ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ዋጋው ውድ ነው! ማንም ሊያራክሰው አይችልም፤ ኢትዮጵያዊነት በጀግንነት፣ በድል አድራጊነት፣ በአልበገር ባይነት፣ በአርቆ አስተዋይነት፣ በፈሪሃ ፈጣሪ አስተዋይነት፣ በተቻችሎ መኖር እና የጠንካራ አንድነት የመጣ እና እዚህ የደረሰ ተምሳሌታዊ የክብር
ስም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የማይደፈር ወኔ፤ የማይነካ ድንበር ነው፤ ለወራሪ የማይንበረከክ፤ ለግፈኞች እጅ የማይሰጥ፤ ለጉልበተኞች የማይተኛ፤ ለሰንደቁ ክብር የሚዋደቅ፤ እምቢ ለሀገሬ ብሎ ታሪክን የሰራ፤ ዛሬም መስራቱን የቀጠለ ነው ብለዋል ወ/ሮ አዳነች፡፡