አፍሪካ ፤ የቱኒዚያ መምህራን የትምህርት ሚኒስትሩ እንዲለቁ ጠየቁ
አርስት ታህሳስ 12 2011
በቱኒዚያ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የደሞዝ ጥያቂያችን መልስ አላገኘም በሚል ምክንያት ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በሺወች የሚቆጠሩት አንጋፋ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ሰልፉን ባካሄዱበት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ሃቲም ቤን ሳሌም ዘርፉን በአግባቡ መምራት ስላልቻሉ ቦታውን ለሌሎች መልቀቅ አለባችው የሚል መፎክር ይዘው ታይተዋል፡፡
ቻናል ኒውስ ኤዢያ እንደዘገበው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተሰባሰቡት መምህራኑ በትምህርት ሚኒስቴር ለፊት ሆነው ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ለመምህራን እና ለመላው ህዝብ እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮሁ ነበር፡፡
የመምህራኑ ጥያቄ የደሞዝ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ሪፎርም እንዲደረግ እና ነፃ የትምህርት እድል እንዲስፋፋ ጭምር የሚያሳስብ ነው፡፡
በቱኒዚያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚያነሱ ዜጎች የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያከሂዱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም፡፡
የመንግስት ሰራተኞች በየጊዜው የደሞዝ ጭማሬ ጥያቄ ቢያነሱም ሀገሪቱ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ስላለባት ጥያቄያቸው መልስ አላገኘምሰ፡፡
ቱኒዚያ በፈረንጆቹ 2016 የበጀት ጉድለቷን ለመሙላት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጠይቃ እንደነበር ይታወቃል፡፡