loading
አዲስ ተሻሚዎቹ የድሬዳዋ ባለስልጣናት ሃገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ እንተጋለን አሉ

 

 

አዲስ ተሻሚዎቹ የድሬዳዋ ባለስልጣናት ሃገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ እንተጋለን አሉ

ሀገር አቀፉን ለውጥ  ማራመድ አልቻሉም የተባሉ 76 አመራሮች ደግሞ ከሥልጣን እንዲነሱ ተደርጓል።

አዳዲሶቹ ሹመቶች ይፋ የተደረጉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አራተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነው።

ምክር ቤቱ በጉባዔው አቶ ሱልጣን አልይን የድሬዳዋ  አስተዳደር ፣ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ፣ ወይዘሮ  ጫልቱ ሁሴንን ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤት ዋና ኦዲተር በማድረግ በሙሉ ድምጽ መርጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤነት በተነሱት  አቶ አብዱሰላም መሐመድ ምትክ   አቶ ከድር ጁሃርን ወደአፈጉባዔነት ወንበሩ አምጥቷል።

አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ከአፈ-ጉባኤነታቸው የለቀቁት በራሳቸው ፍላጎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑም ታውቋል።

በጉባኤው የተሾሙት ባለስልጣናት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ በመመለስ  ሀገራዊ ለውጡን ከዳር እናደርሳለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመመለስ ያቃታቸውና ሃገራዊ ለውጡን መቀጠል ያልቻሉ 76 አመራሮች ከሥልጣን እንዲነሱ ተደርጓል።

27 አመራሮች  ደግሞ አቅማቸው በሚመጥናቸውና የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚባሉበት ቦታ በመመደብ የማሸጋሸግ ሥራ መከናወኑን ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡

ከቀበሌ እስከ ካቢኔ ደረጃ ባሉ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለግሉ በነበሩና አሁን ከስልጣን በተነሱ ግለሰቦች ምትክ ብቃት ያላቸው ወጣት አመራሮች መተካታቸውን ነው ከንቲባው የገለፁት፡፡

አዲሶቹ አመራሮች ሀገር አቀፍና አስተዳደራዊ ለውጡን ለማሳካት  ግንባር ቀደም ሆነው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

እንደከንቲባው ገለጻ ድሬዳዋ ከተማ 60 በመቶ በሚሆኑ አመራሮች ላይ ለውጥ አድርጋለች ።ይህም ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በተሳተፉባቸው መድረኮች የቀረቡትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ወሳኝ  አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

” አመራሩን የመፈተሸና የማጥራት ሥራ ቀጣይነት አለው፤ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ይጠናከራል ” ብለዋል ከንቲባው፡፡ ዜናው የኢዜአ ነው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *